የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት መደረግ ሲጀምሩ የሸገር ደርቢ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ሲዳማ ቡና ስሁል ሽረን አሸንፏል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ተጠባቂ በነበረው እና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በርካታ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ባሳለፉበት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል።
የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ በሆነው በዚህ መርሐግብር ምንም እንኳን እንደ ቀደሙት አመታት ባይሆንም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከተደረጉት ጨዋታዎች አንፃር በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም በሙከራዎች ያልታጀበ ሲሆን በሁለቱም በኩል በተለይም በመስመር በኩል የሚደረጉ የማጥቃት ሂደቶች ውጤታማ አልነበሩም።
- ማሰታውቂያ -
ወደ ግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፍፁም ጥላሁን በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ በበፍቃዱ አለማየሁ ያደረጓቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂዎቹ ተመልሰዋል።
በአጋማሹ ተገኑ ተሾመ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ይዞት የገባውን ኳስ ይዞ ለማለፍ ሲሞክር በበፍቃዱ አለማየሁ ጥፋት ቢሰራበትም የጨዋታው ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዝምታ ማለፋቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ከነበሩት ክስተቶች መካከል የበረከት ወልዴ መጎዳት ሲሆን ተጫዋቹ ለተጨማሪ ህክምና ወድያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ ፉክክር ፣ የተሻሉ የግብ ሙከራዎች እንዲሁም በርካታ ካርዶችም የተመዘዙበት ነበር።
በጨዋታ ረገድ ቡናማዎቹ በአማካይ ክፍል ላይ አሜሪካዊውን ኪሩቤል ደሳለኝ እና ሚኪያስ ፀጋዬን ቀይረው በማስገባት ያደረጉት የተጫዋቾች ለውጥ በተለይም በመሀል ሜዳው ላይ ብልጫ እንዲወስዱ ያስቻላቸው ሲሆን ጠንካራ የግብ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለው ነበር።
በአጋማሹ ዲቫይን ዋቹኩዋ ፣ ኪሩቤል ደሳለኝ ፣ አንተነህ ተፈራ እንዲሁም ሚኪያስ ፀጋዬ ለግብ የቀረቡ ጠንካራ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር።
በተለይም ሚኪያስ ፀጋዬ የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም አንተነህ ተፈራ ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ የወጣበት የግንባር ኳስ ለቡናማዎቹ አስቆጪ የግብ ሙከራዎች ነበሩ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ፍፁም ጥላሁን እና አብዱ ሳሚዮ ቻታኮራ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ያደረጓቸው ጠንካራ ሙከራዎች በዳንላድ ኢብራሂም በግሩም ሁኔታ ግብ ከመሆን ድነዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ በፍፁም ጥላሁን እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥኖች ውስጥ ጥፋት ቢሰራባቸውም በጨዋታው አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ሲወስኑ በነበሩት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዝምታ ታልፈዋል።
ጨዋታው ያለ ግብ ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 29 ያደረሰ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ነጥቡን 23 አድርሷል።
በ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከመቻል በመጪው ቅዳሜ የካቲት 1 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ደግሞ ሲዳማ ቡና ስሁል ሽረን 1 – 0 በማሸነፍ ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።
አመሻሽ 12:00 ጀምሮ በተደረገው የሲዳማ ቡና እና ስሁል ሽረ ጨዋታ ደግሞ የመስፍን ታፈሰ የ50ኛ ደቂቃ ግብ ለአሊቶዎቹ ሶስት ነጥቦችን ለማሳካት በቂ ነበር።
ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 22 በማድረስ በጊዜያዊነት ከ12ኛ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።
ስሁል ሽረ በበኩሉ የውድድር ዓመቱን ስምንተኛ ሽንፈት በማስተናገድ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቆየት ተገዷል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ስሁል ሽረ ከወልዋሎ አዲግራት ይጫወታሉ።


