የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታድየም መደረግ ጀምረዋል።
በቀዳሚው ጨዋታ የተገናኘቱ መቀሌ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ በ2 – 2 ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።
ያሬድ ብርሀኑ በሰባተኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ግብ ምዓም አናብስቱን በጊዜ መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።
ነገር ግን የመቀሌ 70 እንደርታዎች የ1 – 0 መሪነት ለ11 ደቂቃዎች ብቻ ነበር መቆየት የቻለው።
- ማሰታውቂያ -

በ16ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ከግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ከረጅም ርቀት የደረሰውን ኳስ በግንባር በመግጨት አስቆጥሯል።
ያሬድ ብርሀኑ እና አህመድ ሁሴን ያስቆጠሯቸውን ግቦች ተከትሎ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠሯቸውን የግብ ብዛቶች 7 በማድረስ የኮከብ ግብ አግቢነቱን በጋራ መምራት ጀምረዋል።
በ32ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቦና አሊ ያስቆጠረው ግብ መቀሌ 70 እንደርታን ዳግም መሪ አድርጓል።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ 60ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፍቃዱ መኮንን ግሩም የግንባር ኳስ አስቆጥሮ የጨዋታውን ውጤት 2 – 2 አድርጓል።
የዘጠኝ ሰዓቱ ጨዋታ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 23 በማድረስ በግብ ክፍያ በልጦ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በ22 ነጥቦች በነበረበት የ7ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር መቀሌ 70 እንደርታ ከወላይታ ድቻ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች 2 – 0 ረቷል።
ኤፍሬም ታምራት በ88ኛው ኪቲካ ጀማ ደግሞ በ90+5 ደቂቃዎች ላይ የዓምናውን ሻምፒዮን አሸናፊ ያደረጉ ግቦችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበት ሲሆን አዳማ ከተማ በበኩሉ ተከታታይ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደበት ጨዋታ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 18 በማድረስ ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዳማ ከተማ በበኩሉ በ15 ነጥቦች በነበረበት 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።
በ18ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም አዳማ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ።


