By using this site, you agree to the Privacy Policy and Terms of Use.
Accept
ሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያ
  • መነሻ ገፅ
  • ዜናዎች
  • ፕሪሚየር ሊግ
    • ባህርዳር ከተማ
    • ወላይታ ዲቻ
    • ድሬዳዋ ከተማ
    • ፋሲል ከነማ
    • ሲዳማ ቡና
    • አዳማ ከተማ
    • ሀዋሳ ከተማ
    • ቅዱስ ጊዮርጊስ
    • ኢትዮጵያ ቡና
    • ጅማ አባጅፋር
    • ወልቂጤ ከተማ
    • ሰበታ ከተማ
    • ሀዲያ ሆሳዕና
  • ዋልያዎቹ
  • ውድድሮች
  • English Article
  • French Articles
  • ስለ እኛ
Reading: “ትልቁ ግቤ በኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ማልያ ዋንጫ ማሳካት ነው” ማህሌት ምትኩ (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)
Share
Notification Show More
Latest News
ኢትዮጵያ ቡና የፋይናስ ችግር እንገጠመው ተገለፀ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ዜናዎች
“ኢትዮዽያ ቡናን ብትነኩ ከመቃብሬ ተነስቼ አጠፉቹሀለው” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ዜናዎች
ኢንተርናሽናል አርቢትር ማኑኤ ወ/ጻዲቅ ከአዳማ ተሰናበተ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዜናዎች የኢትዮጵያ እግርኳስ ዳኞች ማህበር
በረከት አማረ ወደ ቀደመ ክለቡ ሊመለስ ይችላል ?
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዝውውር ዜናዎች ኢትዮጵያ ቡና ዜናዎች
አርባምንጭ ከተማ ሴኔጋላዊ አማካይ አስፈረመ
የዝውውር ዜናዎች ዜናዎች አርባምንጭ ከተማ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ
Aa
ሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያ
Aa
  • መነሻ ገፅ
  • ዜናዎች
  • ፕሪሚየር ሊግ
  • ዋልያዎቹ
  • ውድድሮች
  • English Article
  • French Articles
  • ስለ እኛ
  • መነሻ ገፅ
  • ዜናዎች
  • ፕሪሚየር ሊግ
    • ባህርዳር ከተማ
    • ወላይታ ዲቻ
    • ድሬዳዋ ከተማ
    • ፋሲል ከነማ
    • ሲዳማ ቡና
    • አዳማ ከተማ
    • ሀዋሳ ከተማ
    • ቅዱስ ጊዮርጊስ
    • ኢትዮጵያ ቡና
    • ጅማ አባጅፋር
    • ወልቂጤ ከተማ
    • ሰበታ ከተማ
    • ሀዲያ ሆሳዕና
  • ዋልያዎቹ
  • ውድድሮች
  • English Article
  • French Articles
  • ስለ እኛ
Have an existing account? Sign In
Follow US
  • Advertise
© 2023 Hatrick Spoert. Design by Tech-ethiopia.com All Rights Reserved.
ቃለመጠይቅዜናዎች

“ትልቁ ግቤ በኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ማልያ ዋንጫ ማሳካት ነው” ማህሌት ምትኩ (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)

Habtamu Mitku
Habtamu Mitku 1 year ago
Share
SHARE

“ለሴቶች ትኩረት ቢሰጥ የበለጠ ውጤት ይመጣል”

“አውሮፓ ውስጥ ዕድል ባገኝ መጫወት የምፈልገው ማድሪድ ነው”

“ሰናይት ቦጋለን ባገኛት ሊጉ ላይ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ እንደምጨርስ አምናለሁ”

 

- ማሰታውቂያ -

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ ደምቀው በመታየት ላይ ካሉ እና ለነገ ተስፋ ተጥሎባቸው ዛሬን ስማቸውን እየተከሉ ካሉት መካከል ቀዳሚዋ ናት።

ትውልዷ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ደብረዘይት ቢሾፍቱ የሆነው ፤ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የ2015 ምሩቅ የሆነቸው ፤ በኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም በዋናው ብሔራዊ ቡድን የተጫወተች ፤ አምና በሲዳማ ቡና ዘንድሮ በኢትዮ ኤሌክትሪክ የደመቀችው ፤ በሁለቱም እግሮቿ በምቾት የምትጫወተው ማህሌት ምትኩ የሳምንቱ የሀትሪክ ስፖርት ድህረገፅ እንግዳችን ናት።

የታላላቆቿን መንገድ ተከትላ ሩቅ በመጓዝ ላይ ያለች በድንቅ ብቃቷ ከሀገር ወጥቶ ከመጫወት ባለፈ በብሔራዊ ቡድን ማልያ ዋንጫ ማሳካት አለብኝ ብላ በቆራጥነት በራሷ ላይ እየሰራች ያለች ናት።

ብዙ ተማርኩበት ስለምትለው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ቆይታዋ ፤ የሲዳማ ቡና ቆይታዋ ፤ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እያሳለፈችው ስላለው ጊዜ ፤ በዕድሜ እርከን እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን የነበራት ቆይታ ፤ ሰለ ሩቅ ሕልሟ ፤ ከአጥቂ ወደ ተከላካይ ከተከላካይ ደግሞ ወደ አጥቂ ስለተመለሰችበት አጋጣሚ እና በሴቶች እግር ኳስ መስተካከል ስላለበት ነገርም የበሰለ አስተያየቷን ተናግራለች።

13 ቁጠር ማልያን የምትለብስበት ከቁጥርነት የዘለለ ትልቅ ምክንያት ፤ በሊጉ አብሬያት ብጫወት የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ እሆናለሁ ስላለቻት ተጫዋች ፤ ከሜሲ እና ከሮናልዶም ያለ ጥርጥር ብላ በቀዳሚነት የጠቀሰችውንም ተጫዋች በቃለ ምልልሱ ገልፃልናለች።

ልዩ ብቃት ፣ የላቀ የራስ መተማመን ፣ ትልቅ ህልም ፣ ለህልም መሳካት ዛሬ መልፋት ፣ ትሁትነት ፣ ከህፃንነት የጀመረ ጠንካራ ሰራተኝነት መገለጫዋ ነው።

ማህሌት ምትኩ አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በተደረገው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር አምስት ግቦችን አስቆጥራለች።

ውድ የሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ ተከታታዮች ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመስመር አጥቂዋ ማህሌት ምትኩ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገናል። እንደታነቡት ተጋብዛችኋል።

ሀትሪክ – እግር ኳስ የጀመረሽበት መንገድ ምን ይመስላል ?

ማህሌት – ወደ ኳስ የገባሁት ታላቅ ወንድም እና እህቴ እግር ኳስ ተጫዋች ነበሩ እና እነሱን በማየት በትምህርት ቤት ተጫወትኩኝ ከዛን በኋላም ቢሾፍቱን በመወከል በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በመሄድ ብዙ ቡድኖች ነበሩ እየሄድኩኝ በመጫወት እግር ኳስን ወደ ራሴ ህይወቴ አስገባሁኝ። እና ደስ ይላል እግር ኳስን በዚህ ሁኔታ በመጀመሬ ደስተኛ ነኝ።

ሀትሪክ – በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የነበረሽ ቆይታ እና ከወጣሽ በኋላ ላለው የእግር ኳስ ሕይወትሽ ምን ያህል ጠቅሞሻል ?

ማህሌት – የአካዳሚ ቆይታዬ በጣም ደስ ይል ነበር። አራት አመታትን ነው የቆየሁት ስገባ በጣም በልጅ ዕድሜዬ ነበር። ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ቢሆንም ግን ከሰው ጋር ስለምግባባ እና ስለምቀላለድ እዛ ደስ ይል ነበር በጣም። ያለው ሁሉ ነገር ደስ ይል ነበር።

በአካዳሚው የተማርኩት ትምህርት ደግሞ ሴት ልጅ ነኝ ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ፤ እነሱን ሁሉ ተጋፍጬ እንዴት ማለፍ እንዳለብኝ ፤ ሁለት ደግሞ አዕምሮዬ ላይ እንዴት ራሴን መገንባት እንዳለብኝ ብዙ አይነት ፈተናዎች ቢያጋጥሙኝ እንዴት ማለፍ እንዳለብኝ የተረዳሁበት ነው።

እንደውም የሆነ ጊዜ የገባን ሰዓት ላይ ከፍተኛ ሊግ ገብተን ነበር እና ሙሉ መሸነፍ ነበር። በመሸነፍ ውስጥ አዕምሮአችን ጠንካራ እንዲሆን እንደዚህ አይነት ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙን እየተመከርን እና አዕምሮአችንን እያሳደግን ቀጣይ አመት በዛ ልክ አስተካክለን። እና በጣም ደስ የሚል የአካዳሚ ቆይታ ነበር።

ከአሰልጣኞቹ እስከ ተጫዋቾቹ ድረስ በምግብ ቤት ባለው ዙሪያ ድረስ በጣም ደስ የሚል ነው ማለት ትህትናቸው የተለየ ነበር። ስርዓት ላለው ልጅ በጣም ደስ የሚል እና ጥሩ ቦታ ነው ስርዓት ለሌለውም ልጅ የሚማርበት እና የሚስተካከልበት ነው። እና በጣም ደስ የሚል የአካዳሚ ቆይታ ነው የነበረኝ።

ሀትሪክ – ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በኋላ ሲዳማ ቡና የተቀላቀልሽበት አጋጣሚ ?

ማህሌት – ሲዳማ ቡና የገባሁበት አጋጣሚ ሀዋሳ ላይ ውድድር ሲደረግ በአሰልጣኜ በኩል ይጠይቁኝ ነበር። ክረምት ላይ አካዳሚ ከተመረቅኩ በኋላ ብዙ ክለቦች ጠይቀውኛል። ከብዙ ክለቦች መካከል ሲዳማ ቡናን ምርጫዬ አድርጌ ክለቡን ተቀላቀልኩ።

ሲዳማ ቡና በቆየሁበት ደግሞ አስተማሪ የሆኑ ነገሮችን ፣ ፈተናዎችን ፣ የመጀመሪያ ክለቤም ስለሆነ እንዴት ማለፍ እንዳለብኝ ብዙ ብዙ አይነት ትምህርቶችን ፣ ስነ ምግባር እና እንዴት ክለብ ላይ ደግሞ ራሴን እንዴት ማስተዳደር እንዳለብኝ እረፍት እንዴት መውሰድ እንዳለብኝ ጨምሮ ብዙ ብዙ ነገሮችን ተምሬ ወጥቻለሁ።

በአጠቃላይ ሲዳማ ቡና ቤት በጣም ደስ የሚል ቆይታ ነበረኝ ያው ከሁለተኛ ዙር በኋላ ውጤቱ አሪፍ ባይሆንም ማለት መሸነፍ እና የአቻ ውጤት ብናስከተልም በጣም ደስ የሚል ቆይታ ነበር ያሳለፍኩት በሲዳማ ቤት።

ሀትሪክ – በሲዳማ ቡና የአንድ አመት ቆይታ ካደረገሽ በኋላ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አመራሽ። ከሌሎች ክለቦች በተለየ ኤሌክትሪክን የመረጥሽበት ምክንያት ምን ነበር ?

ማህሌት – ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የገባሁት አካዳሚ እያለን ከኛ ባች ፊት ለፊት የነበሩት እዛ ይገቡ ነበር። በቢጫ ቴሴራ ምናምን ብቻ እዛ ቤት ያለው ነገር ሁሉ አሰልጣኟ ሴት በመሆኗ ብቻ ራሱ በጣም የመግባት ፍላጎቴ ራሱ እዛ ነበረ። ያለው ነገር በሚሰጡት ትኩረት በብዙ በብዙ ነገሮች የመግባት ፍላጎት ነበረኝ ወድያው ጥያቄ እንደቀረበልኝ(ከዛ በፊት መቻል አቅርቦልኝ ነበረ) እሱን ውድቅ አድርጌ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አቀናሁኝ እና በጣም ደስ የሚል እና አሪፍ ቡድን ነው የገባሁት በጣም ደስ ብሎኛል።

ክለቡም እኔን የመረጠኝ ከአካዳሚ ጀምሮ በሲዳማ ቡና እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ባሳየሁት ብቃት እና ፀባይ ነው ብዬ ነው እኔ የማስበው።

ሀትሪክ – የዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመሪያው አጋማሽ እንዴት ነበር ላንቺ ?

ማህሌት – ብዙም አይደለም። እንደጠበኩት አይደለም። ቡድኔን አገኘዋለሁ ብዬ የሄድኩበት አጋጣሚ ከቤቴ ተነስቼ የወጣሁበት ግብ ላይ ስላላደረስኩኝ ዘንድሮ የመጀመሪያ አጋማሽ ደስ አይልም። ቀጣይ ሁለተኛ ዙር ላይ እንደ ቡድንም አስተካክላለሁ ብዬ አስባለሁ። ያው ብዙዎቻችን አዳዲስ ተጫዋችም ስለሆንን ጊዜ ይፈልጋል ።

ሀትሪክ – በዘንድሮው የውድድር ዘመን በጨዋታ ሂደት ቦታ እየቀያየርሽ ስትጫወቺ ነበር። ይበልጥ ምቾች የሚሰጥሽ የትኛው ቦታ ላይ ስትጫወቺ ነው ?

ማህሌት – በፊት መጫወት የምፈልገው የፊት አጥቂ ቦታ ላይ ነበር ከጊዜ ሂደት በኋላ ደግሞ ወደ መስመር ስወጣ መስመርን ምርጫዬ አደረግኩት እና የመስመር ተጫዋች መሆን ይበልጥ ምቾት የሚሰማኝ ቦታ ነው።

ሀትሪክ – በሁለተኛው ዙር ምን አቅደሻል ? በግልም በክለብም ?

ማህሌት – ሁለተኛ ዙር ላይ እንደ ግል የመስመር አጥቂ ከመሆኔ አንፃር የጎል ዕድሎችን መፍጠር እና ያገኘሁትን የጎል አጋጣሚዎች በመጠቀም አሁን ላይ ካለን የደረጃ ሰንጠረዥ እና ውጤት ቡድኔን ጥሩ ደረጃ ለማድረስ ነው። እንደ ቡድን የሁላችንም አላማ እንደዚህ ነው ዕቅዳችን። ሁለተኛው ዙር ላይ ጥሩ ውጤት ይዘን ለማጠናቀቅ ነው።

ሀትሪክ – ወደ ብሔራዊ ቡድን እንምጣ እስኪ ? ለዕድሜ እርከን እና በዋናው ብሔራዊ ቡድንም መጫወት ችላሻል። ስለ እርሱ ንገሪኝ እስኪ ?

ማህሌት – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጀመሪያ የተጫወትኩት በ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነው። አሰልጣኝ እንዳልክ ይዞት በነበረው እና ታንዛኒያ ላይ በተዘጋጀው ውድድር የተሳተፈው ቡድን ላይ ተጫውቻለሁ።

ከዛ በኋላ ደግሞ አሰልጣኝ ፍሬው በዋናው ብሔራዊ ቡድን ከነ ሎዛ ጋር ጠራኝ ከዛ በኋላ ደግሞ ከ20 አመት በታች እስከ ሞሮኮ ባለው ድረስ ተጫወትኩኝ።

ቀጥሎ ከ17 አመት በታች ደግሞ አሰልጣኝ ራውዳ በያዘችው ቡድን የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ተጫወትኩኝ ማለት ነው እና በብሔራዊ ቡድን በተሰጠኝ ዕድል ተጠቅሜያለሁ።

ሀትሪክ – ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ሲደረገልሽ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብሽ ?

ማህሌት – ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገልኝ ከ17 አመት በታች ነው።ራሴን ብቃቴን ስለማውቀው ምንም አልመሰለኝም ነበር። እንኳን የፊት ተጫዋች ተከላካይ እያለው ራሱ ተጫዋቾች ሲጠሩ ሙሉ የራስ መተማመን ነበረኝ እንደምጠራ ፤ የዛኑ አመት ደግሞ በ19 ግቦች ክብረወሰን ሰብሬ የከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ስለነበርኩ እንደምጠራ እርግጠኛ ሆኜ ራሴን አዘጋጅቼ ነበር። እንደ አዲስ አልሆነብኝም ነበር እና በጣም ቀሎኝ እና ደስ ብሎኝ ስጫወት ነበር በብሔራዊ ቡድን።

ሀትሪክ – ተከላካይ ነበርሽ ማለት ነው ? እንዴት ወደ አጥቂነት ተቀየርሽ ?

ማህሌት – አካዳሚ ልክ እንደገባሁ ኩመራ በቀለ በተከላካይነት ነበረ ያሰለፈኝ። ሶስት አመት ከግማሽ አካባቢ በተከላካይ ቦታ ተጫወትኩ እና በአንድ ጨዋታ በእልህ ተናድጄ ከተከላካይ ተነስቼ የአጥቂ ቦታ ሄድኩና ግብ አስቆጥሬ ባገባሁት ጎል ቡድናችን አሸነፈ። በዛ ሰዓት ነበር መልሼ ወደ በፊት ቦታዬ የተመለስኩት ፤ አካዳሚ ከመግባቴ በፊት ግን አጥቂ ነበርኩ።

ሀትሪክ – በሉሲዎቹ ማልያ ምን ማሳካት ታልሚያለሽ ?

ማህሌት – በብሔራዊ ቡድን ማሳካት የምፈልገው ትልቅ ነገር ነው። የብሔራዊ ቡድን ጥሩ አገልጋይ ሆኜ ሀገሬን ከፍታ ላይ አድርሻት ማለት ጥሩ ደረጃ ላይ ማድረስ ፍላጎት አለኝ።

ሀትሪክ -በእግር ኳስ ሕይወትሽ በጣም የተደሰትሽበት እና ያዘንሽበት አጋጣሚ ?

ማህሌት – እስካሁን ባለው በዘንድሮው የውድድር ዘመን ድሬዳዋ ላይ በመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ ያስቆጠርኩበትን አጋጣሚ ነው። በቃ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር።

መቼም የማልረሳው ደግሞ አይሻለኝም ብዬ ተስፋ ቆርጬ ማለት ሲዳማ ቡና እያለሁ ሁለተኛ ዙር ላይ ከመቻል በነበረን ጨዋታ አዳማ ላይ ተጎድቼ ነበር።የዛን ስሜት አረሳውም መቼም።

ከዛን በኋላ ደግሞ በኔ ምክንያት ሁለት ተጫዋቾችን ጎድቼ ነበረ። ቅድስት ንግድ ባንክ እና ደማ ድሬዳዋ የነበረችው ማለት ያው እግር ኳስ ላይ ያጋጥማል። እና በነዚህ ሶስት ጨዋታዎች ላይ የማልረሳቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረው አልፈዋል።

ሀትሪክ – ጉዳቱ ምን ያህል ከባድ ነበር ?

ማህሌት – አካዳሚ ሶስተኛ አመት ላይ እያለሁ ነው። ከፍተኛ ሊግ የገባን ሰዓት ላይ የጡንቻ መሰንጠቅ ጉዳት አጋጠመኝ እና አንድ ወር ከምናምን ቁጭ አልኩ። በዛን ወቅት ደግሞ ከኳስ አይደለም አንድ ወር አንድ ቀን መራቅ ራሱ በዛ ሰዓት ላይ ያለው ስሜት ከባድ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ የሊጉ ውድድር አዳማ ላይ ሲደረግ ከመቻል ሁለተኛ ዙር ላይ ስንጫወት የብሽሽት ጉዳት አስተናገድኩ። እና ለረጅም ጊዜያቶች እስከ ክረምት ድረስ አልዳንኩም ነበረ። ተቀይሬ በመግባት 5 ወይም 10 ደቂቃ ምናምን እያልኩ እያገገምኩ ነበር ዓመቱን ያጠናቀኩት።

ሀትሪክ – ሴትነት እና እግር ኳስ ምን ያህል ከባድ ነው?

ማህሌት – ሴትነት እና እግር ኳስ በጣም ከባድ ነው። ማለት በኛ ሀገር ነው እንዲከብድ የሆነው የሰዉ አመላካከት ፣ የቤተሰብ አመለካከት ፣ የጎረቤት አመለካከት በጣም ከባድ ነው።እሱ ብቻ ሳይሆን በእግር ኳሱ ላይ ራሱ እኔ እስካሁን አላጋጠመኝም ግን ብዙዎቹ በክልልም ብትሔድ ፣ በፕሪሚየር ሊጉም ብትሄድ ፣ በከፍተኛ ሊጉም ብትሔድ ሴትነትን የሚፈትኑ አመራሮች አሉ። ብዙ አይነት አሰራር አለ በቃ ኳስን ወደኸው እንዳትጫወት የሚያደርጉ ሰዎች አሉ።

በኔ ላይ አልደረሰም ግን በብዙ ጓደኞቼ ታዳጊ እዚ ደብረዘይት ላይ በሚባሉ ነገሮች ላይ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይፈጠራሉ እና ሴትነት እና እግር ኳስ ከባድ ነው።

የሴት ወጉን ትትው ነው አንዳንዶቹ ፤ አሁን እግር ኳስ ሲባል የወንድ ብቻ ስለሚመስላቸው የሴትነት ባህሪዋን ትታ ወደ እግር ኳሱ አለም የምትገባ ሴት አለች።

ሁለት ደግሞ ሴት ምን ብዙ አይነት ፈተና አለባት። ሴት ልጅ ምን ስትሆን ነው የወደፊት መንገዷን የምትመራው የሚሉት ነገሮች ሁሉ ስታ እግር ኳስን ወዳ ብዙ ነገሮችን ትታ ትገባበታለች እና አንዳንዴ በኛ ሀገር ሲሆን ደግሞ በጣም ከባድ ነው። ማህበረሰቡ ካልተቀበለ እንደውም አሁን አሁን እየተስተካከለ ስለሆነ በጣም ደስ ይላል። ግን በመስተካከል ውስጥ ደግሞ ብዙ የተሸፈኑ ገበናዎች አሉ። ሴትነታቸውን ተፈትነው ከእግር ኳሱ የወጡ ሴቶች ብዙ ሴቶች አሉ እና ሴትነት እና እግር ኳስ በጣም ከባድ ነው።

ሀትሪክ – በእግር ኳስ ሕይወትሽ የቤተሰብሽ ድጋፍ ምን ያህል ነው ?

ማህሌት – ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ በቤተሰባችን እግር ኳስ ተጫዋቾች ስለነበሩ ይሄን ያህል ግፊት አልነበረም። ታላቅ ወንድም እና እህቴ ደብረዘይትን ወክለው ተጫውተዋል። ግን እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ ስራ እየሰራን ስለነበረ የተወሰነ ጫና ነበረው። አካዳሚ ራሱ ስንሄድ እኔ እና እህቴ ነበርን የተመለመልነው እና ሁለታችሁ እንኳን ቢደርሳችሁ በዕጣ ነበር ትሄዳላችሁ የተባልነው ፤ እና እንደ አጋጣሚ እኔ ተመርጬ እኔ ሄድኩኝ እንጂ ከቤተሰብ ጋር ይሄን ያህል ቁጣ የሚያስነሳ ነገር አልነበረም ። እንደውም አንዳንዴ ቀምጣ ምናምን ይገዛልን ነበር።

እዚህ ለመድረስ ያበቁኝ ቤተሰቦቼ በመሆናቸውም በጣም ደስ ይለኛል። ይረዱኛል። አባቴም ስለ ኳስ ስለሚያውቅ ለእናቴም ያስረዳታል። በጣም ደስ ይል ነበር በቤተሰብ ዘንድ ያገኘሁት አቀባበል።

ሀትሪክ -በእግር ኳስ ሕይወትሽ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተልሽ ማነው ?

ማህሌት – ይሄ ይሄ ለማለት ይከብደኛል። ደብረዘይት ላይ አራት ሰው ጋር ተጫውቻለሁ ። ነብሶ ፣ ቶማስ ፣ መንጌ እና ሰናይት የምትባል አሰልጣኝ አለች እነሱጋር ስራዬ ብዬ በሚገባ ሰርቻለሁ።

ክረምት ላይ ስመጣ የደብረዘይት ህዝብ ሁሉ ለኔ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል። ወደ ፕሮፌሽናሊዝም ደግሞ መጓዝ ስጀምር ኩመራ በቀለ አለ በአካዳሚ ደረጃ አብዮት እንዲሁም አስናቀ አለ። አካዳሚ እያለሁ ዶክተሮቹ ሳይቀሩ አስተዋጽኦ አበርክተውልኛል።

ብቻ እግር ኳሱ ላይ እግርህን ካስገባህ የሚደግፍህ አይዞህ የሚልህ ሰው አይጠፋም ። በዛው ልክ ደግሞ ቅስምህንም የሚሰብር አትሆንም አንቺ እንዲ ነሽ አንቺ እንዲ ነሽ የሚል አለ እና በእግር ኳሱ ላይ እነዚህን ሰዎች ለኔ ተፅዕኖ ፈጥረውልኛል ብዬ አምናለሁ። አመሰግናለሁ።

ሀትሪክ -እስካሁን ካስቆጠርሻቸው ግቦች በተለየ የምታስታውሺው ወይም ምርጡ ግብሽ ?

ማህሌት – አካዳሚ እያለሁ 2015 ላይ ባህርዳር ላይ ከ16.50 ውጪ ያስቆጠርኩት ግብ አይኔ ላይ ነው። አሁንም ድረስ ማግባት የምፈልገው አይነት ጎል ነበር። ከርቀት ማግባት ደስ ይለኛል እና ተመችቶኛል ለራሴ እና አዳማ ላይም ዘንድሮ በቺፕ ያገባሁት ጎል የማልረሳቸው ጎሎቼ መካከል ናቸው።

ሀትሪክ – ብዙዎች በቀጣይ አመታት ላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደምትደመቂ እና በሉሲዎቹ ማልያ ታሪክ እንደምትሰሪ ይናገራሉ። ስለነዚህ አስተያየቶች ምን ትያለሽ ?

ማህሌት – እንኳን እነሱ ይቅሩና እኔ ራሱ የማስበው ተፅዕኖ እፈጥራለሁ ብዬ የማምን እና ቆርጬ የተነሳሁ ስለሆንኩኝ እንደዚህ በማሰባቸው እና እኔ ላይ ተስፋ በመጣላቸው ደስተኛ ነኝ። ደግሞ ድጋሚ አንተ ያሰብከው እና አዕምሮክ ላይ ያቀድከው ሌላ ሰው እንደዚህ ባንተ ዕምነት ሲጥል ነገ አንተ ትተካለክ ፤ እንዲህ መንገድ ላይ ስሄድ አንቺ ማህሌት ነገ በብሔራዊ ቡድን ትትኪያለሽ ሲሉኝ በጣም ደስ ይለኛል በቃ።

ፍላጎትህ ይበልጣል በቃ ትልቅ ደረጃ እንደምትድረስ ታስባለህ እና እንደዚህ በማሰባቸው እንደዚህ ደግሞ ሞራል ሲሰጡኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ።

አባቴ ራሱ ደውሎ ዘንድሮ መበርታት ነው ብሔራዊ ቡድን ምናምን ሲል በጣም ደስ ይላል። እንደዚህ ተስፋ የተጣለባት ሴት ልጅ በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል። እኔ ራሴን እዚህ ላይ በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል እና ተስፋቸውን እና ዕምነታቸውን ከፈጣሪ ጋር እንዲረዳኝ እና እንዳሳካ ፀሎት በማድረግ ይተባበሩኝ እኔም ደግሞ እዚህ ስራዬን በመስራት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ እጥራለሁ።

ሀትሪክ – ኢትዮጵያውያን ሴት ተጫዋቾች ሎዛ በአሜሪካ ፥ አርያት እና አረጋሽ በታንዛኒያ ብቃታቸው በደንብ እያስመሰከሩ ነው ? የነሱ በዚህ ደረጃ መገኘት ላንቺም ሆነ ለሌሎች ሴት ተጫዋቾች የሰጣችሁ መነሳሳት እንዴት ትገልጪዋለሽ ?

ማህሌት – ገና ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ወደ ውጪ ወጥቼ ስጫወት እኔማ እዚህ መጥቼ መጫወት አያቅተኝም የሚል ራሴ ላይ የገነባሁት ሀሳብ ነበረኝ። እነሱ ወጥተው ሲጫወቱ እነሱ ጎል ሲያገቡ በጎሎች ላይ ሲሳተፉ በጣም ደስ ይለኛል።

በክለብ ራሱ ምግብ ልንበላ ቁጭ ስንል ኧረ እኛማ የመጫወት ዕድል አለን። እንወጣለን። እነሱ መንገዱን ከፍተውልናል እና እንጫወታለን። እነሱ አንዴ ካስጀመሩት እንጫወታለን። ብቻ ብሔራዊ ቡድናችን ውጤት ይኑረው እንጂ ወጥተን የመጫወት አቅም አለን። እየተባባልን እንመካከራለን እና የነሱ መውጣት ለኛ ጥሩ ነገር ነው የፈጠረልን።

ከመነሳሳትም ባሻገር የአፍሪካ ሀገራትም የአውሮፓ ሀገራትም ወደ እኛ እግር ኳስ ዞረው እንዲመለከቱ አድርገውታል እና በጣም ጥሩ ነው።የነሱ መውጣት ለኛ ጥሩ ሆኖልናል።

ሀትሪክ – በእግር ኳስ ትልቁ ግብሽ ምንድነው ?

ማህሌት – በእግር ኳስ ትልቁ ግቤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማልያን ለብሼ ዋንጫ ማሳካት ነው። በቃ ትልቁ አላማዬ በምንም ይሁን በምንም በትንሹም ይሁን በትልቁ የኢትዮጵያን የየሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ወክዬ ዋንጫ ማንሳት ነው።

ከዛ ባሻገር ደግሞ ሀገር ውስጥ ብቻ አይደለም ዕቅዴ ከሀገር ወጥቼ የመጫወት ዕቅድ አለኝ። ይህንንም ደግሞ ከፈጣሪ ጋር አሳካዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ሀትሪክ -ከእግር ኳስ ውጪ ያለሽን ጊዜ በምን ታሳልፊያለሽ ?

ማህሌት – በውድድር ጊዜ ሲሆን መፅሐፍቶችን በማንበብ ፤ በመተኛት ፤ ለኔ የሚጠቅሙኝን ማህበራዊ ድህረ ገፆች(Social Media) በመጠቀም አሳልፋለሁ።

ከውድድር ውጪ ሆነን ደግሞ ከውድድር ውጪ በምንሆንበት ጊዜ ዋና በመዋኘት ፣ ፕሌይ ስቴሽን በመጫወት ፣ ፑል በመጫወት እና ከጓደኞቼ ጋር አብሬ አሳልፋለሁ።

የበዓላት ወቅት ላይ ደግሞ ገጠር ያሉ ቤተሰቦቼ ጋር በመሄድ እዝናናለሁ አልፎ አልፎ ደግሞ የተራራኳቸውን ጓደኞቼን አገኛለሁ።

ሀትሪክ – በሴቶች እግር ኳስ ላይ መስተካከል አለባቸው የምትያቸው ነገሮች ምንምንመ ምንድናቸው ?

ማህሌት – በሴቶች እግር ኳስ ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት። አሁን እየተሰጠ አይደለም እያልኩ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ለወንዶቹ የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ቢሰጥ በእርግጠኝነት እግር ኳሱ እስካሁን ለውጥ ይመጣ ነበረ። አሁንም ለውጥ እየመጣ ነው ግን አሁንም ተጨማሪ ለውጥ ይመጣል።

ሁለተኛው ደግሞ ለሴት የሚሰጠው ቦታ ልክ አይደለም። በአመራር ዘንድም በብዙዎች ዘንድም የሚሰጠው ትኩረት ልክ አይደለም።

አንዳንድ ክለቦች ላይ ለሴት ተጫዋቾች የሚሰጠው በደመወዝም ሆነ በትጥቅ ጉዳይ ምናምን ልክ አይደለም። ለወንዱ የደረሰው ሁሉ ለሴት መድረስ አለበት አሁን ኤልፓ እንደዚህ አይነት ነገር የለም። ማለት ሙሉ ለሙሉ ይሰጥሀል እኩል ነው የምትካፈለው ግን አንዳንድ ክለቦች ላይ ደግሞ እየተቸገሩ ይስተዋላል።

በእግር ኳሱ ላይ ትኩረት መስጠት በቃ በአጭሩ ለሴቶች ትኩረት ቢሰጥ የበለጠ ውጤት ይመጣል። የምንወዳደርባቸው ከተሞች ደግሞ ቢቀያየሩ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማምነው። የአየር ሁኔታውን ለመልመድም የሴት እግር ኳስም እንዲህ አለ እንዴ እንዲባልም ያደርጋል።

ለምሳሌ ዘንድሮ አዲስ አበባ ተቀላቀለ ከአዳማ እና ከሀዋሳ ውጪ ደግሞ ሌሎች ከተሞች ላይ ቢሆን ሰዉም ለሴት እግር ኳስ ያለው አመለካከት እንዲቀየር በክልሎች ያሉ ተጫዋቾችም እንዲነቃቁ እና እንዲጫወቱ እድል ይፈጠራል እና እነዚህ ናቸው ቢስተካከሉ ብዬ የማስበው።

ሀትሪክ – በአውሮፓ የመጫወት ዕድል ብታገኚ መጫወት የምትፈልጊበት ክለብ ?

ማህሌት – አውሮፓ ውስጥ ዕድል ባገኝ መጫወት የምፈልገው ማድሪድ ነው። የማድሪድ ደጋፊ ስለሆንኩ ማድሪድ ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል። ከእንግሊዝ ደግሞ ማንችስተር ዩናይትድ ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል።

ሀትሪክ – በሊጉ ላይ ካሉ ተጫዋቾች አብሬያት ብጫወት የምትያት ተጫዋች ማናት ?

ማህሌት – ወደ ፊት ሰናይት ቦጋለን ባገኛት ሊጉ ላይ ተፎካካሪ ግብ አግቢ ብቻ ሳይሆን አንደኛ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ እንደምጨርስ አምናለሁ። በጣም ደስ የምትል አጥቂዎችን ብቻ እየመገበች የምትጫወት የምመኛት አይነት አማካይ ተጫዋች ናት።በጣም ትመቸኛለች።

ሀትሪክ – መልበስ የምትወጂው ቁጥር ? ለምን ?

ማህሌት – መልበስ የምወደው ቁጥር 13 ነው። የተወለድኩበትም ወር 13ኛ ወር ውስጥ ሲሆን እናም የሩፋኤል ቤተክርስትያን ውስጥ ስላደግኩኝ ነው። የሆነ ጊዜ ላይ ታምሜ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ሄጄ ፀሎት ተደርጎልኝ ነው የዳነኩት። መንትያ እህት ነበረችኝ እና መንትያዬ ስታርፍ እኔ ደግሞ እየተጣጣርኩኝ ነበር። ከዛ እናቴ ተሳለች ሩፋኤል ቤተክርስቲያን በዛን ወቅት ዳንኩኝ ማለት ነው ለዛም ነው 13 ቁጥርን የምለብስበት ምክንያት።

ሀትሪክ – ሜሲ ወይስ ሮናልዶ ?

ማህሌት – ምንም ጥርጥር የለውም። ክርስቲያኖን ነው በጣም የምወደው ለኔ ልዩ ነው። ሜሲም ይችላል ግን ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለኔ በጣም ልዩ ነው።

ሀትሪክ – የምትወጂው ምግብ ?

ማህሌት – ሁሉንም ምግብ እወዳለሁ። በይበልጥ የምወደው ቤተሰብም ያሳደገኝ ክትፎ ነው። ክትፎ በጣም እወዳለሁ። ክትፎ ስፖርተኛ ብዙም አይወድም ግን አሁን ላይ እግር ኳሱ ላይ ከገባሁ በኋላ ማዘውተር ትቻለሁ ግን በጣም የምወደው እሱን ነው። ቅንጬም በጣም እወዳለሁ።

ሀትሪክ – ጠዋት ስትነሺ መጀመሪያ የምታደርጊው ነገር ?

ማህሌት – ጠዋት ስነሳ መጀመሪያ የማደርገው ፀሎት ነው። ከዛ በኋላ ልምምድ ካለ ከፀሎት በኋላ ወደ ልምምድ እሄዳለሁ ልምምድ ከሌለ ደግሞ ቤተክርስቲያን ሄደን እንመጣለን።

ሀትሪክ – ቅፅል ስምሽ ?

ማህሌት – ቅፅል ስም የለኝም ግን ትንሿ ሎዛ ይሉኛል ፣ ሀላንድ ይሉኛል ብዙ አለ CR7ም የሚለኝ አለ። ቅፅል ስም ይሄ አለ የምለው የለም ሁሉም በሚፈልገው ነው የሚጠራኝ።

ሀትሪክ – ከኢትዮጵያውያን ሴት ተጫዋቾች በተለየ የምታደንቂያቸው ?

ማህሌት – ቅድም እንዳልኩህ ሰናይተ ቦጋለ በጣም ትመቸኛለች። በጣም ምርጥ አማካይ ናት።ከአጥቂ ከተባለ ሎዛ አበራ ፣ ሴናፍ ዋቁማ እና ሀና ቶርጋ የምትባል ተጫዋች ነበረች። ሲጫወቱ በጣም ደስ ይሉኛል።

ሀትሪክ -እግር ኳስ ተጫዋች ባትሆኚ ኖሮ ምን ትሆኚ ነበር ?

ማህሌት – ነጋዴ የምሆን ይመስለኛል። በቤተሰብም ስራ እንሰራ ነበረ። ማለት እኛ ቤታችን ብዙ አይነት ስራዎችን እየሰራን ነው ያደግነው። ይሄ ይሄ ነው ብዬ ማብራራት አልችልም። ታዳጊ እያለሁ እንኳን ሳምቡሳ እየሸጥኩ በቆሎ እየሸጥኩ ነበር ያደግኩት እና ነጋዴ የምሆን ይመስለኛል።

ሀትሪክ – በመጨረሻም ማመስገን የምትፈልጊያቸው ካሉ …

ማህሌት – እዚህ ለመድረሴ እዚህ ለመቆሜ ምስጋና ለመድኃኒዓለም እናት ለቅድስተ ድንግል ማርያም ይሁንልኝ። ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። በመቀጠል ቤተሰቤን ፤ ቤተሰቤ ከጎኔ ሆኖ ምን በላሽ ምን ጠጣሽ እያሉ አካዳሚ ሆኜ እንኳን ምግብ በምሳ ዕቃ ቋጥረው ይልኩልኝ ነበር። ቤተሰቤን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። ወንድሞቼን እህቶቼን ታናናሾቼ ሳይቀር ተነሺ ሂጂ ልምምድ ሂጂ እያሉ ያበረታታቱኛል።

የደብረዘይት አሰልጣኞቼን ቅድም የጠቀስኳቸው እነ ቶማስ ፣ መንጌ ፣ ሰናይት ፣ መሐመድ ፣ ፍሬው ፣ ኤርሚያ(ነብሶ) በጣም ነው የማመሰገንናችሁ ክበሩልኝ።

አካዳሚ በነበርኩበት ሰዓት ላይ ደግሞ እነ አስናቀ ፣ ኩመራ በቀለ ፣ አብዮት በጣም ነው የማመሰግነው እና እዛ ያሉ ሙሉ የአካዳሚ ተጫዋቾች እና ሰራተኞች በጣም ነው የማመሰግነው።

አሁን ላይም በውስጥ መስመርም ስማችሁን ያልተጠቀስኩም ሰዎች በጣም ነው የማመሰግናችሁ ክበሩልኝ።

ሀትሪክ – አመሰግናለሁ ።

ማህሌት – አመሰግናለሁ።

You Might Also Like

ኢትዮጵያ ቡና የፋይናስ ችግር እንገጠመው ተገለፀ

“ኢትዮዽያ ቡናን ብትነኩ ከመቃብሬ ተነስቼ አጠፉቹሀለው” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

ኢንተርናሽናል አርቢትር ማኑኤ ወ/ጻዲቅ ከአዳማ ተሰናበተ

በረከት አማረ ወደ ቀደመ ክለቡ ሊመለስ ይችላል ?

አርባምንጭ ከተማ ሴኔጋላዊ አማካይ አስፈረመ

Share this Article
Facebook Twitter Email Print
By Habtamu Mitku
Follow:
Writer at Hatricksport
Previous Article ኤፍሬም ኃይለማርያም፣ ግሩም ሃጎስ፣ ብርሃኑ አዳሙ እና ብሩክ እንዳለ የጨዋታ እገዳ ተጣለባቸው
Next Article ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ድል ሲመለስ መቀሌ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

Follow US

Find US on Social Medias
127k Like
2.9k Follow
1.6k Follow
19.7k Follow

Weekly Newsletter

Subscribe to our newsletter to get our newest articles instantly!

ተነባቢ ዜናዎች
ዜናዎችኢትዮ-ኤሌክትሪክየጨዋታ ዘገባቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግለገጣፎ ለገዳዲ

የጨዋታ ዘገባ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለገጣፎ ለገዳዲን በሶስት ግብ ልዩነት ረቷል

Habtamu Mitku By Habtamu Mitku 3 years ago
የጨዋታ ዘገባ | ሲዳማ ቡና የ3 ለ 0 ድል ተጎናፅፏል
“ተጨዋቾቻችን የሀገር ክብር ሊረዱ ይገባል” /አሰልጣኝ ውበቱ አባተ/
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለስፖርት ሚድያ አካላት በኢአፌ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
Exclusive interview with |ዮርዳኖስ አባይ ሁሌም ንግስና የለም ሪከርዱ ቢሰበር በጣም ደስተኛ ነኝ!!! 
- Advertisement -
Ad imageAd image
Global Coronavirus Cases

Confirmed

0

Death

0

More Information:Covid-19 Statistics
about us

Phone: 0993808668 Email: [email protected] .

Find Us on Socials

© Hatrick Sport 2023 All Rights Reserved.

Removed from reading list

Undo
 

Loading Comments...
 

    Welcome Back!

    Sign in to your account

    Lost your password?