የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ ከድል የራቁ ቡድኖች ወደ ድል የተመለሱበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
በቀዳሚው የዕለቱ ጨዋታ በሻምፒዮንነት ፉክክሩ ላይ ያለው ሀድያ ሆሳዕናን የገጠመው ወልዋሎ አዲግራት ድል ቀንቶታል።
የውድድር ዘመኑን ቀዳሚ ድል ከ14 ጨዋታዎች በኋላ ያገኘው ወልዋሎ አዲግራት የማሸነፊያ ግቡን በቡልቻ ሹራ አማካኝነት አግኝቷል።
ክለቡ ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ ያሸነፈው ከአምስት አመታት በፊት ታህሳስ 29 2012 ዓ.ም ድሬዳዋ ከተማን ነበር።
- ማሰታውቂያ -
የሊጉን ግርጌ የያዘው ቡድኑ ነጥቡን ወደ አምስት ማሳደግም ችሏል።
ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ ድል አድርጎ ከመሪው ኢትዮጵያ መድኅን በነጥብ እኩል የሚሆንበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ቡድኑ ሽንፈት ያስተናገደውም ከስምንት(7 ድል እና 1 አቻ)ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ነው።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር ወልዋሎ አዲግራት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲጫወት ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድኅን ጋር ይጫወታል።
በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ደግሞ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ አሸንፎ የማያውቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቶታል።
ሲዳማ ቡናን የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2 – 0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ሁለቱንም ግቦች ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በ21ኛ እና 24ኛ ደቂቃዎች ላይ አስቆጥሯል።
የዘሪሁን ሸንገታው ቡድን ፋሲል ከነማን ከረታበት የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ያሳካው የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ነው። ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን 18 ማድረስም ችሏል።
ሲዳማ ቡና በበኩሉ ከሶስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ሽንፈትን ያስተናገደበት ጨዋታ ሆኗል። ቡድኑ በነበረው 19 ነጥብም ለመቆየት ተገዷል።
በቀጣይ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልዋሎ አዲግራት ሲጫወት ሲዳማ ቡና በበኩሉ አራፊ ቡድን ነው።


