የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታድየም መደረግ ጀምረዋል።
በቀዳሚው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ወላይታ ድቻን አሸንፏል።
2 – 1 በተጠናቀቀው ጨዋታ አዞዎቹ በያሬድ ዳርዛ የ16ኛ ደቂቃ ግብ እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ መሪ መሆን ችለዋል።
በረጅም ወደ አርባምንጭ ከተማ የሳጥን ክልል የተላከውን ኳስ የቡድኑ ተከላካዮች በተገቢው መልኩ ለማራቅ በተቸገሩበት አጋጣሚ ያገኘው ያሬድ ዳርዛ በግብ ጠባቂው ላይ ከፍ አድርጎ ከመረብ አሳርፎታል።
- ማሰታውቂያ -
ጨዋታው 60ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ አህመድ ሁሴን ከቡድን አጋሩ የተላከለትን ኳስ የግብ ክልሉን ለቆ በወጣው አብነት ሀብቴ አናት ላይ ከፍ በማድረግ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
መደበኛው ዘጠና ደቂቃ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ በቀረው ጊዜ አህመድ ሁሴን በድጋሚ ግብ አስቆጥሮ አዞዎቹን አሸናፊ አድርጓል።
አጥቂው ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በቀኝ እግሩ ተቆጣጥሮ በግራ እግሩ በመምታት ከመረቡ አዋህዶታል።
ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 21 በማድረስ ደረጃውን ወደ 6ኛ ከፍ ሲያደርግ ወላይታ ድቻ በበኩሉ ወደ 7ኛ ደረጃ ተንሸራቷል።
በ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ መቀሌ 70 እንደርታ እንዲሁም ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ደግሞ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት የዓምናው ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከስሁል ሽረ 1 – 1 ተለያይተዋል።
በጨዋታው 60ኛ ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጀማ ከባሲሩ ዑመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር በመግጨት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።
ነገር ግን የንግድ ባንክ መሪነት ከአምስት ደቂቃዎች መሻገር አልቻለም።
በ65ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረን ኳስ መሀመድ ሱሌማን በግንባሩ በመግጨት ስሁል ሽረን አቻ ያደረገ ሲሆን ጨዋታውም በ1 – 1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ሁለቱም ቡድኖች ነጥባቸውን በአንድ ከፍ ቢያደርጉም በደረጃቸው ላይ ግን ለውጥ ማድረግ ሳይችሉ በነበሩበት ለመቆየት ተገደዋል።
በ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዳማ ከተማ ሲጫወት ስሁል ሽረ አራፊ ቡድን ነው።


