የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዕለቱ በቀዳሚነት ከቀን 9:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ የተገናኘቱ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ነጥብ ተጋርተዋል።
በጨዋታው ናትናኤል ዘለቀ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ መነሻውን ባደረገ ኳስ ባስቆጠረው ግብ ወልዋሎ አዲግራትን መሪ ማድረግ ችሏል።
ወልዋሎ አዲግራት በመሪነት የመጀመሪያውን አጋማሽ ቢያጠናቅቅም የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ 48ኛው ሰከንድ ላይ ግብ አስተናግዷል።
- ማሰታውቂያ -
ግቡን ያስቆጠረው እስራኤል እሸቱ ሲሆን የውድድር ዓመቱ ቀዳሚ ግቡ ሆኖም ተመዝግቧል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ አሸንፎ ደረጃውን ማሻሻል የሚችልበትን ዕድል ባለመጠቀሙ በ11 ነጥቦች በነበረት የ17ኛ ደረጃ ለመቆየት ሲገደድ ወልዋሎ አዲግራትም ነጥቡን 2 አድርሶ የ18ኛ ደረጃውን ይዞ ቀጥሏል።
በ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ይጫወታሉ።
የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ፋሲል ከነማን ከመቻል አገናኝቶ በተመሳሳይ 1 – 1 ተጠናቋል።
በረከት ደስታ በ38ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ግብ ጦሩን መሪ ሲያደርግ እስከ 70ኛው ደቂቃ ድረስም ጨዋታው በ1 – 0 ውጤት ቆይቷል።
በ70ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከነማው አንዋር ሙራድ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ አየር እንዳለ በመቀስ ምት በመምታት በድንቅ ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል።
ውጤቱንም ተከትሎ መቻል ዳግም ወደ መሪነት የሚመለስበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
መቻል በጨዋታው ባገኘው አንድ ነጥብ አማካይነት ነጥቡን 26 በማድረስ የሁለተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ፋሲል ከነማ በበኩሉ ነጥቡን 17 በማድረስ ወደ 12ኛ ከፍ ብሏል።
በቀጣይ ሳምንት በሚደረጉ ጨዋታዎች መቻል ከባህርዳር ከተማ ሲገናኝ ፋሲል ከነማ አራፊ ቡድን ነው።
ሊጉን ኢትዮጵያ መድኅን ፣ መቻል እና ሀድያ ሆሳዕና ተመሳሳይ 26 ነጥቦችን ይዘው በግብ ክፍያ በመበላለጥ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ስሁል ሽረ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።


