የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ ስታድየም ተደርገዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ አዳማ ከተማ በቀድሞ አሰልጣኙ ከሚመራው ድሬዳዋ ከተማ ተገናኝተው በአንድ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
በጨዋታው መሀመድኑር ናስር በ23ኛው ደቂቃ ላይ በደጋፊዎቹ ፊት የሚጫወተውን ድሬዳዋ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል።
ነገር ግን የድሬዎች ደስታ ብዙም ሳይቆይ በ24ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም አይተን አዳማ ከተማን አቻ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል።
- ማሰታውቂያ -
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግብ ያላስመለተው ጨዋታው በ1 – 1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱንም ተከትሎ ሁለቱም ክለቦች ነጥባቸውን በተመሳሳይ ስምንት አድርሰዋል።
በሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም አዳማ ከተማ ከመቻል ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሀዋሳ ከተማን 2 – 1 ረቷል።
በጨዋታው የተቆጠሩት ሶስቱም ግቦች በሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች የተቆጠሩ ናቸው። 8ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማ መሪ ሲሆን አሊ ሱሌማን ግቡን ያስቆጠረው ተጫዋች ነው።
አቻ ለመሆን እስከ 36ኛው ደቂቃ ድረስ ለመጠበቅ የተገደዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በረከት ሳሙኤል በራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ 1 – 1 ሆነዋል።
በጨዋታው 90ኛ ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊ ሆኗል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥቡን ዘጠኝ አድርሶ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በሰባት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ አራፊ ቡድን ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከፋሲል ከነማ ይጫወታል።


