በፕሪሚየር ሊጉ የሶስተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል።
የአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬው ቡድን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ከተጋራው ቡድን ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ይታገሱ ታሪኩን በስንታየሁ ዋለጬ ተክተው ጨዋታውን ሲጀምሩ በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ ከስሁል ሽረ ነጥብ ከተጋራው ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ግርማ በቀለ እና ቢንያም በላይ በበረከት ሳሙኤል ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና ተባረክ ሄፋሞ ተተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
በጨዋታው ቀዳሚ ደቂቃዎች ላይ ሀዋሳ ከተማ ኳሱን በማንሸራሸር በተለይም በመስመሮች በኩል በግራ መስመር ባደላ መልኩ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል በፈጣን እና በቁጥር አነስተኛ በሆኑ የኳስ ቅብብሎች በሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
- ማሰታውቂያ -
የጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሲደረግ አምበሉ ራምኬል ጀምስ በጨዋታው ጅማሮ ሰከንዶች ውስጥ ከማዕዘን የተሻገረን ኳስ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ሞክሮ ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
በሶስተኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ይዘው የገቡትን ኳስ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በአጋጣሚው አሊ ሱሌማን እየገፋ ይዞ የገባውን ኳስ በግብ ጠባቂው ተጨርፎ ሲመለስ ኳሱን በቅርበት ያገኘው ግርማ በቀለ አልጠቀመበትም።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የሀዋሳ ከተማዎችን የኳስ ምስረታ ስህትት ተጠቅሞ በሳጥኑ ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት የተገናኘው አንተነህ ተፈራ በማይታመን መልኩ ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ልኮታል።
ጨዋታው 24ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቀዳሚው ግብ ተቆጥሯል። በፍቃዱ አለማየሁ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ሞክሮ በተከላካዮች ተደርቦ በሳጥን ውስጥ የቀረውን ኳስ ወንድማገኝ ሀይሉ በተገቢው መልኩ ከግቡ ለማራቅ ሲቸገር የደረሰበት ኮንኮኒ ሁዛፍ ኳስና መረብን አገናኝቷል።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም በፍቃዱ አለማየሁ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በተደጋጋሚ በተለይም በቢንያም በላይ አማካይነት ሲደረጉ የነበሩ ተደጋጋሚ ጥረቶች ጠንካራ አደረጃጀት በነበረው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ ክፍል በቀላሉ ሲበላሽ ቆይቷል።
ከግቡ በኋላ በይበልጥ ጨዋታውን ተቆጣጣሮ የቀጠለው ኢትዮጵያ ቡና ውጤቱን አስጠብቆ የመጀመሪያውን አጋማሽ አጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ገና ከጅማሮው ቶሎ ቶሎ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሳጥን መድረስ የቻለው ሀዋሳ ከተማ በ47ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሆነበትን ግብ አግኝቷል።
ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ እስራኤል እሸቱ ለአሊ ሱሌማን አቀብሎት የ2016 የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አሊ ሱሌማን ኳስና መረብን አገናኝቷል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል አስቀድሞ ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠር ጥረቶች ሲደረጉ የቡናማዎቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ነበር። ነገር ግን ሙከራዎቻቸው ያን ያህል ሰይድ ሀብታሙን የፈተኑ አልነበሩም።
76ኛው ደቂቃ ላይ ግን ራምኬል ጀምስ ከበፍቃዱ አለማየሁ የተሻገረለትን የማዕዘን ኳስ ነፅ ሆኖ በማግኘት ኳስና መረብን አገናኝቷል።
ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም የሀዋሳ ከተማ የተከላካይ መስመር ስስነት በታየበት አጋጣሚ ተቀይሮ የገባው ዳዊት ሽፈራው የኢትዮጵያ ቡናን 3ኛ ግብ አስቆጠሯል።
በመጨረሻም ቡናማዎቹ የውድድር ዓመቱ ቀዳሚ ድላቸውን ነጥባቸውንም አራት ያደረሱበትን ውጤት አስመዝግበው ወጥተዋል።
ኢትዮጵያ ቡናን ከያዘ በኋላ በፕሪሚየር ሊግ እና በኢትዮጵያ ዋንጫ ሀዋሳ ከተማን በአራት ጨዋታዎች የገጠመው ነፃነት ክብሬ በአራቱም ማሸነፍ ችሏል።
በአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።