በፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት ስምንተኛ መርሐግብር ሲዳማ ቡና መቻልን 2 – 1 አሸንፏል።
መቻል በቀዳሚው ጨዋታ ፎርፌ ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን በጨዋታው ሊጠቀማቸው የነበሩ ተጫዋቾች ላይ ለውጥ ሳያደርግ ዘደ ጨዋታው ገብቷል። በሲዳማ ቡና በኩል በሀዋሳ ከተሣ ከተረቱበት ጨዋታ አምስት ለውጦች በማድረግ መስፍን ሙዜ ፣ ፍራኦል መንግስቱ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ ኢማኑኤል ላርዬ እና ይገዙ ቦጋለን በመክብብ ደገፉ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ ብርሀኑ በቀለ ፣ አበባየሁ ሀጂሶ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ተክተው ገብተዋል።
ተጠባቂ የነበረው ጨዋታ ቀዳሚውን ግብ ሲያስተናግድ ሁለት ደቂቃዎች እንኳን ሳይሞሉ ነበር። ግቡ የተቆጠረው በሲዳማ ቡና በኩል ሲሆን ሀብታሙ ታደሰ ከመስፍን ታፈሰ የደረሰውን ኳስ በመጠቀም ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል።
ፈጣን ግብ ያስተናገዱት መቻሎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ወደ አቻ ለመምጣት ተደጋጋሚ ጫና መፍጠር ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
በተለይም ከአቤል ነጋሽ እና በረከት ደስታ እግር ስር በሚነሱ ኳሶች ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ደጋግመው የሲዳማ ቡናን የግብ ክልል ፈትሸዋል። በተጨማሪም አማካይ ላይ የተጣመሩት ሽመልስ በቀለ እና አብዱልከሪም ወርቁ በድንቅ እንቅስቃሴዎች ታጅበው ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ አድርገዋል።
በ11ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ለሽመልስ በቀለ ቀንሶት ሽመልስ ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በሲዳማ ቡና በኩል በቁጥር ባነሱ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።
በተለይም በ21ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ አራት ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ፊት ይዞ ለመሄድ የሞከረውን ኳስ ሬድዋን ናስር አግኝቶ ለይገዙ ቦጋለ በግሩም ሁኔታ አቀብሎት ይገዙ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
በ23ኛው ደቂቃ ላይ ግን መቻል አቻ የሆነበትን ግብ አግኝቷል። አብዱልከሪም ወርቁ በግሩም እይታ ያቀበለውን ኳስ አቤል ነጋሽ ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ለሽመልስ አቀብሎ አንጋፋው ተጫዋች ሽመልስ ኳስና መረብን አገናኝቷል።
ከአቻነት ግቡ በኋላ በሁለቱም በኩል ፈጣን እንቅስቃሴዎች ሲቀጥሉ በተለይም መቻሎች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን አድርገው በጨዋታው ኮከብ በነበረው የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መስፍን ሙዜ ተመልሰዋል።
በ31ኛው ደቂቃ ላይ በረከት በግራ መስመር ይዞ የገባውን ወደ ግብ ሞክሮ በመስፍን ሲያዝበት በ37ኛው ደቂቃ ላይ የበረከት ፣ ሽመልስ እና አብዱልከሪም ድንቅ ጥምረት በታየበት አጋጣሚ የተሞከረው ኳስ ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ከአንድ ደቂቃ በኋላም አብዱልከሪም ወርቁ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ በጠንካራ ምት ወደ ግብ ሞክሮ መስፍን ተቆጣጥሮታል።
ከሙከራ ለደቂቃዎች ርቀው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ሬድዋን ከፍቅረየሱስ ተክለብርሀን ጋር ጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል አድርጎ ባደረገው ሙከራ ዳግም መሪ ለመሆን ሞክረዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች በቀሩበት ወቅት አለምብርሀን ይግዛው በግንባር ሞክሮ በድጋሚ በግብ ጠባቂው ተመልሷል።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከጅምሩ አበባየሁ ሀጂሶን በኢማኑኤል ላርዬ ተክተው የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።
51ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ቀዳሚው የአጋማሹ የግብ ሙከራ እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፍያን ተመልሷል።
መቻሎች በይበልጥ ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት በአንድ ሁለት ቅብብሎች ወደፊት ለመድረስ ቢጥሩም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ደቂቃዎችን መታገስ የግድ ብሏቸው ነበር።
በ61ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል መንግስቱ በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ፍቅረየሱስ ነፃ ሆኖ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ያደረገው ሙከራ ኢላማውን መጠበቅ አልቻለም።
በ69ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡና ተደጋጋሚ ማጥቃት ፍሬ አፍሮቶ ዳግም መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ከቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ ተቀብሎ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በአለምብርሀን ይግዛው ተጨርፎ ከመቻል መረብ ላይ አርፏል።
ከግቡ በኋላ የተጫዋቾች ለውጥን በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን ያደረጉት መቻሎች ቀደም ካሉት የአጋማሹ ደቂቃዎች በተሻለ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል።
በ76ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከርቀት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በመስፍን ሙዜ በአስደናቂ ብቃት ግብ ከመሆን ድኗል።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም አብዱ ሙታላቡ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ያደረገው ጥረት በግብ ጠባቂው ተመልሷል።
በቀጣዮቹ የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ መቻሎች የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጫና ቢፈጥሩም የሲዳማ ቡና ተከላካዮች እና ድንቅ የነበረው መስፍን ሙዜ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ጨዋታውን አጠናቀዋል።
በመጨረሻም አሊቶዎቹ መቻልን 2 – 1 በመርታት ወደ ድል የተመለሱበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
በሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው መስከረም 22(ረቡዕ) ምሽት 1:00 ጀምሮ መቻል ከወላይታ ድቻ እንዲሁም በተከታዩ ቀን መስከረም 23(ሀሙስ) ምሽት 1:00 ሲዳማ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።