በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ መቀመጫቻውን በሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ሲዳማ ቡናን ከሀዋሳ ከተማ አገናኝቶ በሀዋሳ ከተማ የ1 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ሆነው በተጋጣሚ ሜዳ ላይ አብዛኛውን የጨዋታ አጋማሽ ማሳለፍ ችለዋል። በተጨማሪም ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠርም አንፃር ከሀዋሳ ከተማ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በይበልጥ ከኳስ ውጪ ሆነው የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ ሲያሳልፉ በሚነጠቁ ኳሶች በፈጣን ወደ ፊት በመድረስ የሲዳማ ቡናን የኋላ መስመር ለመፈተን ሞክረዋል።
የሲዳማ ቡና አብዛኛው የማጥቃት እንቅስቃሴ በነበረበት የቀኝ መስመር በተለይም ከብርሀኑ በቀለ እና ሬድዋን ናስር በሚጣሉ ኳሶች አሊቶዎቹ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
- ማሰታውቂያ -
በ10ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ የግብ ሙከራ አድርጎ የነበረው መስፍን ታፈሰ ከሰከንዶች በኋላ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በተመሳሳይ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል።
አበባየሁ ሀጂሶ በ13ኛው እንዲሁም መስፍን ታፈሰ በ27ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጓቸው ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች ግብ ጠባቂውን ሰይድ ሀብታሙን የፈተኑ አልነበሩም።
በጨዋታው 20ኛ ደቂቃ ላይ በሀዋሳ ከተማ በኩል የቀኝ መስመር ተከላካዩ እንየው ካሳሁን ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በሲሳይ ጋቾ ተቀይሮ ወጥቷል።
በ34ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው አምበል ያሬድ ባየህ ወደ ፊት ገፍቶ በመምጣት ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ በረከት ሳሙኤል በግንባር ገጭቶ ወደ ራሱ መረብ ልኮት የነበረ ቢሆንም ግቡን ለቆ ወቶ የነበረው ሰይድ ሀብታሙ ተቆጣጥሮታል።
የሲዳማ ቡናን የማጥቃት ሂደት በማቋረጥ ተጠምደው የቆዩትና የተጋጣሚያቸውን የሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመር መፈተን ያልቻሉት ሀይቆቹ በ42ኛው ደቂቃ ላይ በመጀመሪያ ሙከራቸው ግብ አስቆጥረዋል።
እስራኤል እሸቱ በቀኝ መስመር ይዞ የሄደውን ኳስ በጥሩ ዕይታ ለተባረክ ሔፋሞ አቀብሎት ተባረክ ሔፋሞ ኳሱን ከመረብ አሳርፎታል።
በዚህ ግብም ሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት አጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና ጫና ፈጥሮ የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ሲጥሩ እስከመጨረሻው የዳኛው የጨዋታ ማገባደጃ የፊሽካ ድምፅ ድረስ ቆይተዋል።
በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሩትን ግብ አስጠብቀው ለመውጣት በሚመስል መልኩ ሙሉ ለሙሉ የግብ ክልላቸውን ሲከላከሉ ቆይተዋል።
የአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራ በ58ኛው ደቂቃ ሲደረግ መስፍን ታፈሰ ወደ ግብ ያሻገረው ኳስ በአብዱልባሲጥ ከማል ተጨርፎ ሀብታሙ ታደሰ አግኝቶ በግንባር በመግጨት ወደ ግብ ሞክሮ ሰይድ እና የግቡ ቋሚ ኳሱን መረብ ላይ ከማረፍ አግደውታል።
በ67ኛው ደቂቃ ላይም መስፍን ታፈሰ ከአበባየሁ ሀጂሶ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥኑ መግቢያ ሆኖ ግሩም ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ሰይድ ሀብታሙ በግሩም ብቃት ግብ እንዳይሆን አድርጎታል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በተለይም የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ላይ አጥቂው አሊ ሱሌማን ተደጋጋሚ ኳሶችን ቢያገኝም ኳሱን የሚያገኝበት ቦታ ከግቡ ያለው ርቀት እና አጋዥ ተጫዋች በማጣት ተደጋጋሚ ኳሶች ተበላሽተውበታል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ የተጨመሩት አምስት ደቂቃዎች ሊጠናቀቁ ሰከንዶች በቀሩበት ወቅት ይገዙ ቦጋለ በግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ቀንሶ ለኪፕሩቭ ለማቀበል ሲሞክር በረከት ሳሙኤል ኳሱን ተከላክሏል።
በመጨረሻም ሀዋሳ ከተማ በ1 – 0 ውጤት የጨዋታው አሸናፊ ሆኖ አጠናቋል።
በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው መስከረም 17(አርብ) ረፋድ 3:30 ሀዋሳ ከተማ ከስሁል ሽረ እንዲሁም መስከረም 18(ቅዳሜ) 10:00 ሲዳማ ቡና ከመቻል ይጫወታሉ።