በሊጉ የአንደኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀዳሚ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በሶስቱ አዲስ ፈራሚዎቹ ግቦች 3 – 1 አሸንፏል።
በመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን ጠንከር ያሉ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ከማድረግ አንፃር ግን እምብዛም ነበር።
በተደጋጋሚ ከተስተዋሉ የሚቆራረጡ ኳሶች በኋላ በ29ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ አለሙ ከሽመክት ጉግሳ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ አግኝቶ ወደ ግብ ቢልከውም በቀላሉ በግብ ጠባቂው ተይዟል።
ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ የሽመክት እና ፍቃዱ ጥምረት ሲደግም ናትናኤል ናሴሮ ደርሶ ሙከራውን ተከላክሏል።
- ማሰታውቂያ -
ጨዋታው 33ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የጦና ንቦቹ መሪ መሆን ችለዋል። ያሬድ ዳርዛ ከአብነት ደምሴ የደረሰውን ኳስ ከመስመር ወደ ሳጥን በመግባት ለካርሎስ ዳምጠው ለማቀበል ሲሞክር ጌታሁን ባፋ በራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል።
በቀጣዩቹ ደቂቃዎች ላይ ወላይታ ድቻዎች በተለይም ለግቡ መቆጠር መንስኤ በነበረው ያሬድ ዳርዛ አማካኝነት ተጨማሪ እድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው መሪዎች ወላይታ ድቻዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ አጋማሹን ጀምረዋል።
አጋማሹ በተጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳርዛ ከቀኝ መስመር ያቀበለው ኳስ በብሰራት መለሰ እና ብዙአየሁ ሰይፈ አልፎ አብነት ደምሴ ወደ ግብ ቢሞክረውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
ከዚህ ሙከራ ሰባት ደቂቃዎች በኋላ የጨዋታው ውጤት ወደ አቻነት ተቀይሯል። ወላይታ ድቻዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት በመከላከል በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ያመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሀብታሙ ሸዋለም ብልህነት ታክሎበት በእዮብ ገብረማርያም አማካኝነት ድንቅ ግብ አስቆጥረዋል።
ነገር ግን የኢትዮ ኤሌክትሪክ ደስታ ከአራት ደቂቃዎች መሻገር አልቻለም። ፍፁም ግርማ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ተስፋዬ መላኩ በግንባር በመግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን ዳግም መሪ አድርጓል።
ከዚህ ግብ በኋላም ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግም ጭምር የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴን ለማድረግ ጥረቶችን አድርገዋል።
ቡድኑ በረጃጅም ኳሶችም የወላይታ ድቻን የተከላካይ መስመር የሚያልፉ ኳሶችን በመጣል የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ቢጥሩም በቀላሉ ጠንካራ ሙከራዎችን ለማድረግ አልቻሉም።
በ61ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነቱን ግብ ያስቆጠረው እዮብ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ኢላማውን ስቶ ወጥቷል።
በራሳቸው ሜዳ ላይ በቁጥር በርከት ብለው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በፈጣን እንቅስቃሴዎች በተለይም ከመስመር ወደ ግብ ክልል በሚሻገሩ ኳሶች ተጨማሪ ግቦችን ለማከል ሲሞክሩ ተስተውሏል።
በተለይም በ67ኛው ደቂቃ ላይ ብስራት መለሰ ከግራ መስመር ወደ መሐል የቀነሰውን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው ከግቡ ትይዩ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ጨዋታው 84ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አምበል ሽመክት ጉግሳ ከዋና ዳኛው ጋር በነበረው የቃላት ልውውጥ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በጦና ንቦቹ በኩል መሳይ ሰለሞን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ግዙፉ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው በአስደናቂ የመቀስ ምት ከመረብ አሳርፎታል።
አጥቂው በ90ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ የማስቆጠር ዕድልን ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
የዋና ዳኛው ዳንኤል ግርማይ የጨዋታ ማጠናቀቂያ የፊሽካ ድምፅ ሲጠበቅ ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ጥሩነህ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል።
ለደጋፊዎቻቸው የዘመን መለወጫ በዓል የሶስት ነጥብ ያበረከቱት ወላይታ ድቻዎች ከሁለት በላይ ግቦችን አስቆጥረው በሊጉ ድል ሲያደርጉ ከ32 ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታዎች መስከረም 16(ሀሙስ) ምሽት 1:00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም መስከረም 18(ቅዳሜ) ምሽት 1:00 ወላይታ ድቻ ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።