የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት አራተኛ መርሐግብር ባህርዳር ከተማን ከወልዋሎ አዲግራት አገናኝቶ ፍፁም አለሙ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ የጣና ሞገዶቹ ሶስት ነጥቡን ወስደዋል።
ምሽት 1:00 ጀምሮ የተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ቀዝቀዝ ባለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢጀምርም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ የግብ ዕድሎችን ለመመልከት ችለናል።
በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በሚመራው ባህርዳር ከተማ በኩል በተለይም በመስመሮች ከወንድወሰን በለጠ እና ቸርነት ጉግሳ በሚነሱ ኳሶች የወልዋሎ አዲግራትን ተከላካይ ለመፈተን ችለዋል።
በ11ኛው ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማዎች ቀዳሚውን የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ፍፁም አለሙ የወልዋሎ አዲግራትን የኳስ ምስረታ አቋርጦ ያገኘውን ኳስ አቤል ማሙሽ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በግብ ጠባቂው በረከት አማረ በቀላሉ ተመልሷል።
- ማሰታውቂያ -
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት የተገኘውን ኳስ ፍፁም አለሙ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ በድጋሚ በበረከት እጆች ላይ አርፏል።
በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ወልዋሎ አዲግራቶች በተለይም ወደ ፊት ገፍቶ የሚመጣውን የባህርዳር ከተማ የኋላ መስመር በፈጣን ቅብብሎሽ ሰብሮ በማለፍ እድሎችን ለመፍጠር ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርጉም ውጤታማ አልነበሩም።
ቡድኑ በአጋማሹ ቀዳሚውን የግብ ሙከራ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ያደረገ ሲሆን ዳዋ ሆጤሳ ከፍሬው ሰለሞን የነጠቀውን ኳስ ከቡልቻ ሹራ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ግብ ቢሞክርም ሙከራው ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመግባት የተሻሉ ሆነው የቀጠሉት ባህርዳር ከተማዎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት በግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ በአቤል ማሙሽ በኩል አልፎ ፍፁም ወደ ግብ አክርሮ ቢመታውም ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል።
ጨዋታው 25ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የባህርዳር ከተማዎች ተደጋጋሚ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ግብ አስቆጥረዋል። ፍሬው ሰለሞን ከዳዋ ሆጤሳ የነጠቀውን ኳስ ወንደወሰን በለጠ በቀኝ መስመር ይዞ በመግባት ለፍፁም አለሙ አቀብሎት ፍፁም ከመረብ አሳርፎታል።
ከመቻል የሁለት አመታት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ባህርዳር ከተማ የተመለሰው ፍፁም አለሙ የካቲት 21/2014(936 ቀናት በኋላ) ኢትዮጵያ ቡና ላይ ካስቆጠረው ግብ በኋላ በባህርዳር ከተማ መለያ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ሙጂብ ቃሲም በረጅም የመታውን ኳስ በረከት አማረ ከግቡ ክልሉ ወጥቶ በተገቢው ያላራቀውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ አግኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል እምብዛም ሳቢ ያልሆነ እና ከሙከራዎች የራቀ የጨዋታ ክፍለ ጊዜን አሳልፈዋል።
በወልዋሎ አዲግራት በኩል ጨዋታውን በአማካይ ስፍራ ጀምሮ የነበረው ዳዋ ሆጤሳን በፊት አጥቂነት በመጠቀም ለርሱ በሚደርሱ ኳሶች ዕድል የመፍጠር ፍላጎት ቢያሳዩም የረባ የግብ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም።
በባህርዳር ከተማ በኩል በ78ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከመስመር ይዞ ገብቶ የቀነሰውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ቢያገኘውም በውሳኔ ችግር ዕድሉን መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።
ከሁለት ደቂቃዎች በኀላ ወንድወሰን በለጠ ከፍሬው ሰለሞን የደረሰውን ኳስ የግብ ጠባቂው በረከት አማረን መውጣት ተከትሎ ከፍ አድርጎ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል።
በመጨረሻም የፍፁም አለሙ ብቸኛ ግብ ጨዋታው በባህርዳር ከተማን የ1 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው መስከረም 17(አርብ) 10:00 ላይ ወልዋሎ አዲግራት ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ምሽት 1:00 ጀምሮ ባህርዳር ከተማ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ።