በሊጉ ሁለተኛ መርሐግብር በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት የተጨመወተው ድሬዳዋ ከተማ ሽኩቻዎች በበዙበት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማን አሸንፏል።
በጨዋታው በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ ይበልጥ ኳስ ይዞ በመንቀሳቀስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥር ተስተውሏል።
ቡድኑ በቁጥር በርከት ብሎም የአርባምንጭ ከተማን የተከላካይ መስመር በመፈተን ኳስ እና መረብን ለማገናኘት የነበሩት ጥረቶች በጠንካራ ሙከራ ለመታጀብ በርካታ ደቂቃዎችን አስጠብቋል።
አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ ከኳስ ውጪ ያሳለፉት አርባምንጭ ከተማዎች በሁለት አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ሲደርሱ በተለይም 10ኛው ደቂቃ ላይ ያመከኑት ዕድል አስቆጪ ነበር።
- ማሰታውቂያ -
የግራ መስመር ተከላካዩ ካሌብ በየነ ያሻገረውን ኳስ አህብዋ ብሪያን ከግቡ ትይዩ አግኝቶ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ቢልከውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
ድሬዳዋ ከተማዎች ከአርባምንጭ ከተማ የተከላካይ መስመር ጀርባ በሚጣሉ እና በተለይም በቀኝ መሰመር በኩል በሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ደጋግመው ጥረዋል።
ብርተካናማዎቹ በ30ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ የአንድ ሁለት ቅብብል የአርባምንጭ ከተማን የተከላካይ መስመር በመስበር ኳስን ከመረብ አዋህደዋል።
በጥሩ ፈጣን ቅብብል በቀኝ የሳጥኑ የቀኝ ሳጥን አቅጣጫ ገብቶ መሐመድኑር ናስር ቢደርስውም ኳሱ አምልጦት ሊወጣ ሲል በግሉ ጥረት ኳሱን ለቻርለስ ሙሴጌ አቀብሎ አጥቂው ቡድኑን መሪ አድርጓል።
የመጀመሪያው የጨዋታው አጋማሽም በድሬዳዋ ከተማ የ1 – 0 መሪነት ተጠናቋል።
በርካታ ሽኩቻዎች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች እና ሁለት ግቦች ያስተናገደው አጋማሹ ልክ እንደቀዳሚው ጨዋታ ሁሉ የቀይ ካርድም አስመልክቶናል።
በአጋማሹ ዳግም ሊጉን የተቀላቀሉት አርባምንጭ ከተማዎች ከፊት ቡድኑን ለሚመራው አህመድ ሁሴን ተደጋጋሚ ኳሶችን በማድረስ በአጥቂው አማካይነት ወደ አቻ ለመምጣት ጥረዋል።
ጠንካራው አጥቂ አህመድ ሁሴንም በሚደርሱት ኳሶች በተደጋጋሚ የድሬዳዋ ከተማን ተከላካዮች እጅጉኑ ፈትኗል።
በ47ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂውን አልፎ ጭምር ለማስቆጠር ቢሞክርም አህመድ ረሺድ ደርሶ ግብ ከመሆን አድኖታል።
ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት አዞዎቹ በ54ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ እንዳልካቸው መስፍን ለአሸናፊ ተገኝ ያቀበለውን ያለቀለት ኳስ አሸናፊ ሳይደርስበት ቀርቷል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩልም በተለይም ከመጀመሪያው አጋማሽ በአንፃራዊነት ከነበረው የቀኝ መስመር እንቅስቃሴ ወደ ግራ በማጋደል
ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ሳጥን ለማድረስ ጥረቶች አድርገዋል። ሆኖም ግን በአርባምንጭ ከተማ በኩል በአህመድ ሁሴን እንደሚፈጠሩት አይነት ጠንካራ የግብ ሙከራዎች ለማድረግ ረጅም ደቂቃዎች ለመጠበቅ የግድ ብሏቸዋል።
በአዞዎቹ በኩል በ66ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ በድጋሚ በቀኝ አቅጣጫ ያገኘውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ ተቆጣጥሮታል።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ በጀሚል ያዕቆብ አማካይነት ያደረጉት የግብ ሙከራ ኢላማውን መጠበቅ አልቻለም።
የአህመድ ሁሴን ጥረት በ80ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ ሲያፈራ አጥቂው ከእንዳልካቸው መስፍን የደረሰውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ከመረብ አሳርፏል።
በጨዋታው አልፎ አልፎ የነበሩት ሽኩቻዎች ይበልጥ እየጎሉ በመጡበት የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች በርካታ ክስተቶችን አስመልክተውናል።
የአቻነቱ ግብ ከተቆጠረ አምስት ደቂቃዎች በኋላ ብርቱካናማዎቹ ዳግም መሪ ሆነዋል። በዚህ ግብ ለድሬዳዋ ከተማ ቀዳሚ ግብ መቆጠር አቀባይ እና አስቆጣሪ የሆኑት ተጫዋቾች ሚና ተለዋውጠው ቡድናቸውን መሪ አድርገዋል።
በግራ መስመር የነበረው የመጀመሪያው ግብ አስቆጣሪ ቻርለስ ሙሴጌ ከአቡበከር ሻሚል የደረሰውን ኳስ ወደ መሐል ሲቀንሰው መሐመድኑር ናስር አስቆጥሮታል።
ግቡ በተቆጠረበት ወቅት በጨዋታው ዋና ዳኛ ያልተገባ ባህሪ ያሳየው አበበ ጥላሁን በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በ87ኛው ደቂቃ ላይ አርባምንጭ ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ይዘው የገቡትን ኳስ ግብ ጠባቂው ከግቡ ርቆ ወጥቶ አብዩ ካሳዬ በመለሰበት ወቅት በእጁ ነክቷል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞዋቸውን ገልፀዋል።
በዚህ አጋጣሚ ድሬዳዋ ከተማዎች በፈጣን ይዘው የገቡትን ኳስ መሐመድኑር ናስር ግብ ጠባቂው ኢድሪስ ኦጎዶጆን አልፎ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ኳስና መረብን ማዋሀድ ሳይችል ቀርቷል።
በ90ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉጌታ ካሳሁን እንዲሁም በ90+6 ላይ አህመድ ሁሴን ወደ ግብ ያደረጓቸው ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች የአብዩ ካሳዬን እጆች ማለፍ አልቻሉም።
በመጨረሻም ድሬዳዋ ከተማ በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እየተመራ የመክፈቻ ጨዋታውን በ2 – 1 ድል ፈፅሟል።
በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መስከረም 15 ቀን 10:00 አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ መድኅን እንዲሁም መስከረም 18 ምሽት 1:00 ጀምሮ ድሬዳዋ ከተማ ከወላይታ ድቻ ይጫወታሉ።