የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀዳሚ ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታን ከሀድያ ሆሳዕና አገናኝቶ ሄኖክ አርፊጮ በ9ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው የፍ.ቅ.ም ግብ ነብሮቹ 1 – 0 አሸንፈዋል።
በተከታታይ ሁለት አመታት የመክፈቻ ጨዋታዎች ላይ በመቻል የተሸነፉት ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ መክፈቻ ጨዋታ ድል ተመልሰዋል።
ከጨዋታው በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች የሆኑት ግርማ ታደሰ እና ፀሐዬ ዳንኤል ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ቡድናቸው ድል ያደረገላቸው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የመጀመሪያ ጨዋታ ማሸነፍ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው የሰራናቸው ስህተቶች እስከመጨረሻው ድረስ በጫና እንድጨርስ አስገድደውናል ብለዋል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ግርማ ስለ ስህተቶቹም እንዲህ ብለዋል “አጀማመራችን ጥሩ ነው። ነገር ግን የሳትናቸው ኳሶች አሉ። እነሱን አነሳስተናቸዋል። እንጂ ሁለት ሶስት ኳሶች የማስቆጠር እድል አግኝተናል። ያ ነው መጨረሻ ድረስ ዋጋ ያስከፈለን።”
የቡድናቸው እንቅስቃሴ በፈለጉት ልክ እንዳልነበረ ያነሱት አሰልጣኝ ግርማ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታቸው መበላሸቱን በተለይም አስጨናቂ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተሰናበተ በኋላ የመከላከል አጨዋወትን ስለመከተላቸው ተናግረዋል።
የመጀመሪያ አጋማሽ ስህተቶችም ለሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ያልነበረ እንቅስቃሴ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
አክለውም ቡድናቸው በሽግግር ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ማስተካከል ከቻለ የተሻለ ነገር መስራት እንደሚችሉ ገልፀዋል።
“የመከላከል ጨዋታችን ሁሌም ጥሩ ነው። ለተጋጣሚያችን ዕድል ሰጥተን አንጫወትም። ነገር ግን ሽግግር ላይ ችግር አለብን። ከመከላከል ወደ ማጥቃት ከማጥቃት ወደ መከላከል ትንሽ ክፍተቶች አሉ ዛሬም ያየውት እሱን ነው። እነዛን ካስተካከልን የተሻለ ነገር መስራት እንችላለን።”
የመስመር ተጫዋቾቻቸው ፈጣን ቢሆኑም ኳሶች ግን በተፈለገው መልኩ ሲደርሷቸው እንዳልነበር በመጥቀስ የኳስ ሽግግሮቹ ፈጣን እንዲሆኑ እንሰራለን ብለዋል።
የመቀሌ 70 እንደርታው ዋና አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በውጤቱም በጨዋታው እንቀስቃሴም ደስተኛ እንዳልነበሩ ሲናገሩ በተለይም ኳስ ሲይዙ በራሳቸው ሜዳ ላይ ተነስተው ወደ ፊት ቢደርሱም በተጋጣሚ የግብ ክልል አካባቢ የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ እንዳልነበር ገልፀዋል።
“ያሰብነውን የጨዋታ እንቅስቃሴ ለመከተል ሞክረናል። ተጫዋቾቻችንም ስትራቴጂውን ለመተግበር ሞክረዋል። በሰው ሜዳ ላይ ተጭነን ለመጫወት ብንሞክርም እንዲወጡ ወይም ረጃጅም ኳሶች እንዲጠቀሙ ፈቅደናል። እኛ የገጠምነው ቡድን በመስመር ረጃጅም ኳሶች መጠቀም የሚፈልግ ቡድን ነው። ያንን ወይ ከመነሻው ማስቆም ሁለተኛ ከጀርባ የሚጣሉ ኳሶች መከላከል ነበር።እዛጋር ያለንን ስህተት ተመልክተው ሲያጠቁን ነበር።”
አሰልጣኝ ዳንኤል አክለውም የመከላከል ቅርፃቸው ጥሩ እንዳልነበረ ሲያነሱ በነበሯቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይም ተመሳሳይ ችግር እንደነበር በመጥቀስ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም የፈረሰ ነበር ሲሉ የተከላካይ ክፍላቸውን ተችተዋል።
በተለይም ከቀይ ካርዱ በኋላ ከፊት በቁጥር በመብዛት ጭምር ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም ውጤታማ መሆን አለመቻላቸውንም ጨምረው አንስተዋል።