የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2017 ዓመተ ምህረት ውድድር በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ ከተማ በድሬዳዋ ስታድየም መካሔድ ጀምሯል።
በውድድር አመተ ቀዳሚ ጨዋታ ከአራት አመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው መቀሌ 70 እንደርታ ከሀድያ ሆሳዕና ተገናኝተው ሀድያ ሆሳዕና 1 – 0 አሸንፏል።
በጨዋታው በሁለቱም በኩል በክፍት ጨዋታ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲጥሩ ነብሮቹ ገና በ9ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሆነዋል።
- ማሰታውቂያ -
እዮብ አለማየሁ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የመታውን ኳሰ ቦና አሊ በሳጥን ውስጥ ሆኖ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሔኖክ አርፊቹ ከመረብ አሳርፏል።
በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ተጋጣሚያቸው መቀሌ 70 እንደርታዎች ከኋላ ኳስ መስርተው እንዳይወጡ ተጭነው በመጫወት በነጠቋቸው ኳሶች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል።
በተለይም በ27ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ግርማይ ለኪሩቤል ኃይሉ በማቀበል ከግብ ክልላቸው መስርተው ለመውጣት ሲጥሩ መለሰ ሚሻሞ ነጥቆ ለእዮብ አለማየሁ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም እዮብ ወደ ግብ የመታው ኳሰ በግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ ተይዟል።
ከዚህም ባለፈ መሰል ጥፋቶችን የመቀሌ 70 እንደርታ ተጫዋቾች ቢሰሩም የነብሮቹ ደካማ አጨራረስ ተጨማሪ ግቦችን ከማስቆጠር አግዷቸዋል።
በመቀሌ 70 እንደርታ በኩል ከግብ ክልላቸው ለመውጣት ሲቸገሩ የቆዩ ሲሆን በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ የሚነጠቋቸው ኳሶች ግን በተጋጣሚ ፈጣን መልሶ ማጥቃት የተከላካይ መስመራቸውን ሲፈተን ቆይቷል።
በአንፃሩ በአጋማሹ በተለይም ሰለሞን ሀብቴ በ11ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ የሀድያ ሆሳዕና ግብ ጠባቂ ያሬድ በቀለ በግሩም ሁኔታ አውጥቶታል።
በ35ኛው ደቂቃ ላይ የአብስራ ተስፋዬ በተመሳሳይ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ መቀሌ 70 እንደርታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ የሀድያ ሆሳዕናን የመከላከል መስመር ለመስበር ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርገዋል።
በተለይም የሀድያ ሆሳዕናው አስጨናቂ ፀጋዬ በ54ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተሰናበተ በኋላ ምዓም አናብስቱ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ለማድረግ ሞክረዋል።
አሰልጣኝ ዳንኤል ፀጋዬም ከጨዋታ ቅርፅ ለውጥ እስከ ተጫዋቾች ቅያሪ ድረስ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሊያፈራላቸው አልቻለም።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል በአጋማሹ በይበልጥ በመከላከል ላይ ጥንቅቄ በመውሰድ በሚነጠቁ ኳሶች ፈጣን ተጫዋቾቻውን ለመጠቀም ጥረዋል።
በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ 11 ሙከራዎችን ቢያደርጉም ከሁለት ሙከራዎች የበለጠ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
በዚህም በተለየ ፍጥነቱ የሚታወቀው ተመስገን ብርሀኑ በሶስት አጋጣሚዎች ሁለት ኢላማቸውን የጠበቁ እና አንድ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣ የግብ ሙከራዎችን አድርጓል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ መለሰ ሚሻሞ ከሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
በመጨረሻም ሀድያ ሆሳዕና ከተከታታይ የሁለት አመታት የመክፈቻ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ በድል ጨዋታውን አጠናቋል።
በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መስከረም 16 ቀን 10:00 ጀምሮ መቀሌ 70 እንደርታ ፋሲል ከነማን ሲገጥም ሀድያ ሆሳዕና በሳምንቱ አሬፊው ቡድን ነው።