በአቤኔዘር አበበ
አዳማ ከተማ ድል ሲቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ፣ እንዲሁም ባህርዳር ከተማ ከ መቻል ነጥብ ተጋርተዋል

አዳማ ከተማ 2–0 ሀዋሳ ከተማ
በመጀመሪያው አጋማሽ አዳማ ከተማ የጨዋታ ብልጫ ወስዳ የተሻለ እንቅስቃሴ ብትታይም ወደ ግብ መቀየር አልቻሉም። ሀዋሳ ከተማም ግልጽ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግራ ታይቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማ ጫናውን በማሳደግ የጨዋታ ብልጫዋን ቀጥሏል። በ54ኛው ደቂቃ ብሩክ ታደለ በአዳማ ከተማ ተጫዋች በአቡበከር ሳኒ ላይ በፈጸመው ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ቢንያም አይተን ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አደረገ።አዳማ ከተማ ጫናውን በመቀጠል በ84ኛው ደቂቃ በሀዋሳ ከተማ ተጫዋች ቹኩውብኳ አንቶኒ በራሱ ላይ ያስቆጠረው ግብ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ግቦች አሳደገ። በመጨረሻም አዳማ ከተማ 2–0 በማሸነፍ ሙሉ ሦስት ነጥቦችን ወስዳለች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 0–0 ወላይታ ድቻ
በመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ እላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ሲታይ፣ ወላይታ ድቻ በተደጋጋሚ ወደ ግብ አካባቢ ቢደርስም የግብ ዕድሎቹን ወደ ግብ መቀየር አልቻለም። የመጀመሪያው አጋማሽ 0–0 ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽም ጨዋታው ብዙም ሳይለወጥ ቀጥሏል። ሁለቱም አሰልጣኞች የጨዋታውን ሂደት ለመቀየር ቅያሪዎችን ቢያደርጉም የግብ ልዩነት መፍጠር አልቻሉም። በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስና ወላይታ ድቻ ያለ ግብ ነጥብ ተጋርተዋል።
ባህርዳር ከተማ 0–0 መቻል
በመጀመሪያው አጋማሽ ሽግግሮች በበዙበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች እላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ እረፍት ወጥተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ 0–0 ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች የኳስ ቁጥጥርን በመቀያየር ቢጫወቱም ግልጽ የግብ ዕድሎችን በብዛት መፍጠር አልቻሉም። ጨዋታው በመጨረሻ 0–0 በሆነ ውጤት ሲጠናቀቅ ባህርዳር ከተማና መቻል አንድ አንድ ነጥብ ተጋርተዋል።
አስተያየት ይስጡ