በሊጉ የሳምንቱ የማሳረጊያ ቀናት ሦስት ጨዋታዎች በኢትዮጵያ መድን ፣ ባህርዳር ከተማ እና ነገሌ አርሲ አሸናፊነት ተጠናቀዋል።

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአምናው ሻምፒዮን ኢትዮጵያ መድን ሽንፈት አስተናግዷል። በንፅፅር በይበልጥ ኢትዮጵያ መድኖች የተሻሉ በነበሩበት ጨዋታ ጎል የተቆጠረው ጨዋታው ሊጠናቀቅ ስምንት ደቂቃ ሲቀር ነበር። 82ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ዕይታ ከግራ መስመር ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ በመጀመሪያ ንክኪው ሳመኤል ሳሊሶ አላዛር መርኔ መረብ ላይ በማሳረፍ መድኖች 1ለ0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብለው እንዲቀመጡ ማድረግ የቻሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ሌላኛው በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በአማራ ደርቢ ፋሲል ከነማ እና ባህርዳር ከተማ የተገናኙበት ጨዋታ በባህርዳር ከተማ የሁለተኛ አጋማሽ ሁለት ጎሎች ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ ፔፕ ሰይዶ ከራሱ ሜዳ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል የካሜሮናዊውን የግብ ዘብ ሞይስ ፖዎቴን ከግብ ክልሉ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ግሩም ጎልን የቀድሞው ክለቡ ላይ አስቆጥሯል።
ጨዋታው ቀጥሎ 69ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል አስጀምሮ ወደ ቀኝ የሰጠውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አደም አባስ አመቻችቶለት ብሩክ ሰሙ በቀላሉ ወደ ሳጥን ገፍቶ ገብቶ በማስቆጠር ጨዋታው በጣናው ሞገዶቹ 2ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል።

በሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ነገሌ አርሲ ወሳኝ ድልን በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ላይ አሳክቷል። ጨዋታው 39ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበደ እና ዳዊት ገብሩ ከተጋጣሚ እግር ነጥቀው በመጨረሻም ዳዊት በጥሩ ዕይታ አሾልኮ ያቀበለውን የሮሆበት ሰላሎ የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ስምኦን ማሩ ቢጫዎቹን መሪ አድርጓል። አጋማሹ ሊገባደድ በተጨመረው ጭማሪ 45+8ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ የቅጣት ምት ኳስ ሮሆበት አክርሮ መቶ በተከላካይ ተጨርፋ የደረሰችውን ኳስ ገብረመስቀል ዱባለ ወደ ጎልነት በመለወጥ ሰጎኖቹን አቻ ማድረግ ችሏል።

ጨዋታው ሲቀጥል 55ኛው ደቂቃ ላይ ነገሌ አርሲዎች ከመመራት ተነስተው አሸናፊ የሆኑባትን ጎል አግኝተዋል። ቦና ቦካ ከቀኝ ወደ ሳጥን ያሻማለትን ኳስ ኪቲካ ጂማ በግንባር ገጭቶ ጆኤሎ ሙታክብዋ መረብ ላይ አስቀምጧት ጨዋታውን ነገሌ አርሲዎች 2ለ1 አሸንፈዋል።
አስተያየት ይስጡ