በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሀግብር ወላይታ ድቻ እጅግ ወሳኝ ድልን ሀድያ ሆሳዕናን 1ለ0 በመርታት ሲያረጋግጥ ሀዋሳ ከተማ ከሸገር ከተማ ፣ መቻል ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራት ችለዋል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሳሩ ውሀ በመቋጠሩ ከተያዘለት ደቂቃ ሰላሳዎቹን ዘግይቶ ልክ 7፡30 ሲል የጀመረው የወላይታ ድቻ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ ወላይታ ድቻን እጅግ ወርቃማ ሦስት ነጥብን ያስጨበጠ ድል ተገኝቷል። 40ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ቴዎድሮስ ታፈሠ ከግራው የሜዳ ክፍል የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ሳጥን ሲያሻማ መልካሙ ቦጋለ በደርሶ መልስ ጨዋታ በግንባር ጎል አስቆጥሮ የአመቱን አራተኛ ጎሉ አድርጓታል።

ጨዋታው 1ለ0 በጦና ንቦቹ አሸናፊነት መጠናቀቅ ሲችል ቡድኑም በይበልጥ ከነበረበት ወራጅ ቀጠናው በይበልጥ የወጣበትን ዕድል ሲያስመዘግብ ሀድያ ሆሳዕና በበኩላቸው ቀስ እያሉ ወደ ታች መንሸራተት ችለዋል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ላይ መቻልን ከአዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ መቻሎችን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ለመጠጋት በሜዳቸው የሚጫወቱት አዳማ ከተማዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር የሚገናኙበት ቢሆንም ጨዋታው ጎል ሳይቆጠርበት 0ለ0 ተጠናቋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማን ከሸገር ከተማ አገናኝቶ የነበረው ጨዋታ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተደምድሟል። ሀዋሳ ከተማዎች በሙከራ ረግድ ሻል ባሉበት አጋማሽ 43ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ብሩክ ታደለ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ጎል ልኳት ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ከእጁ አምልጣው መረቡ ላይ ኳሷ አርፋ ሐይቆቹ መሪ ሆነዋል።

ጨዋታውን እየመሩ የቀጠሉት ሀዋሳ ከተማዎች መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት 87ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ከራሳቸው ሜዳ ሸገሮች ያሻገሩትን ኳስ ሚሊዮን ሐይሉ በግንባር ጨርፎ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ይስሀቅ ገብረክርስቶስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ጨዋታው 1ለ1 ሲጠናቀቅ ለሀዋሳ አስረኛ አቻቸው መሆን ችሏል።

አስተያየት ይስጡ