የጎል ፌሽታ በነበረው ጨዋታ ከድል መልስ የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በወልዋሎ ሲሸነፍ ሀድያ ሆሳዕና ከመቐለ ፣ ንግድ ባንክ ከአርባምንጭ ፣ ነገሌ አርሲ ከፋሲል ከነማ ጋር ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

ከቀትር መልስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዘጠኝ ቢጫ እና ሁለት ቀይ ካርዶች በተመዘዙበት ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ በእጁ ለማስገባት ሊጠናቀቅ ሰከንዶች እየቀሩ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገዷል። ከመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ ጊዜ አኳያ በሁለተኛው የተሻለ እንቅስቃሴን ያሳየን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 49ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የተነሳችን ኳስ ፍፁም አለሙ በጥልቀት ይዞ ገብቶ ለብርሀኑ ሰጥቶት አጥቂው በአግባቡ ያመቻቸለትን ኬኔዲ ገብረፃዲቅ ሳጥኑ ውስጥ ያገኛትን ኳስ ቆንጆ ጎል በማድረግ ሞዓም አናብስቱን ቀዳሚ አድርጓል።

ጎልን ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ ለማጥቃት የዳዱት ነብሮቹ መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ ድራማዊ ክስተት ማስተዋልን የቻልን ሲሆን 90+3 የሀድያ ሆሳዕናው ተከላካይ ዳግም ወንድሙ ፍፁም አለሙ ላይ ጥፋት ሰርተሀል በሚል በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ በዕለቱ ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ከወጣ በኋላ 90+7ኛ ደቂቃ ላይ ቡድኑ በጎዶሎ ተጫዋች አቻ ሆኗል። ከእጅ ውርወራ ወደ ውስጥ የተሻማች ኳስን በመቐለ ተከላካይ በጭንቅላት ተገጭታ ከሳጥን ውጪ የደረሰች ኳስን ፀጋአብ ግዛው እጅግ አስገራሚ ጎል በማድረግ ጨዋታውን ወደ 1ለ1 ያደረገ ሲሆን አምበሉ ሔኖክ አርፊጮም በደስታ አገላለፁ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ ጨዋታው 1ለ1 ተደምድሟል።

ሌላኛው የአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናገደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ እንዲሁም በአዳማ የተደረገው የነገሌ አርሲ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በተመሳሳይ ያለ ጎል 0ለ0 ተደምድሟል።

የስድስት ጎሎች ድራማን ያሳየን የኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጨዋታ በወልዋሎ 4ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ገና 4ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ ከግራ ሳጥን ውስጦ መነሻዋን ያደረገች ኳስን ሰጥቶት ጋናዊው አጥቂ ኮንኮኒ ሀፊዝ በግራ እግሩ በቀደመ ክለቡ መረብ ላይ ጎል ቢያስቆጥርም ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን ቡናማዎቹ አቻ ሆነዋል። አቡበከር አዳሙ ራሱ ያስጀመረውን ኳስ በመጨረሻም ወደ ጎል መቶ ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ ጆኤል ሙታክብዋ ሲመልሳት ዲቫይን ዋቹኩዋ በድጋሚ አግኝቶ የሰጠውን አቡበከር አዳሙ ጎል አድርጓታል። ጨዋታው ቀጥሎ 12ኛው ደቂቃ ዲቫይን ዋቹኩዋ ከራሱ ሜዳ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ በረከት ብርሀኑ በአግባቡ በመቆጣጠር በመጨረሻም ቆንጆ ጎል አድርጎ ቡናማዎቹን ወደ መሪነት ቢያሻግርም 38ኛው ደቂቃ በጨዋታው ሲደምቅ ከነበረው ዳዊት ገብሩ የደረሰውን ኳስን ከሳጥን ውጪ አጥቂው ያሬድ ከበደ ግሩም ጎልን በዳላንድ ኢብራሂም መረብ ላይ አስቀምጦ አጋማሹ 2ለ2 ተጋምሷል።
ከዕረፍት መልስ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሜዳ መመለስ የቻሉ ሲሆን 54ኛው ደቂቃ ላይ ግን እንዳልካቸው ጥበቡ ከቀኝ ሰብሮ የሰጠውን በየነ ባንጃው በቀድሞው ክለቡ መረብ ላይ ወልዋሎን ወደ መሪነት ያሸጋገረች ጎል ሲያስቆጥር 90ኛው ደቂቃ የቡናማዎቹ ግብ ጠባቂ ዳላንድ ኢብራሂም በሁለት አጋጣሚ በሰራው ጥፋት በጫና ውስጥ ኳስን ያገኘው ኮንኮኒ ሀፊዝ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛዋን ጎል ያለፈው አመት ክለቡ ላይ አስቆጥሮ ወልዋሎ 4ለ2 አሸንፏል።
አስተያየት ይስጡ