የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀናቶች ዕረፍቱ ሲመለስ ኢትዮጵያ መድን እና መቻል ወሳኝ ድል ሲያሳኩ ሸገር ከተማ ከወላይታ ድቻ አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል።

የሳምንቱ የመክፈቻ መርሀግብር ወደ ሊጉ መሪ ሀዋሳ ከተማ ከፍ ለማለት ኢትዮጵያ መድን ደግሞ በሊጉ ለመክረም ወሳኝ በነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም የቀትር መርሀግብር ሀዋሳ ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉት 7ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ሽመልስ በቀለ ከማዕዘን አሻምቶ ተባረክ ሄፋሞ በግንባር ገጭቶ ጎል ቢያስቆጥርም ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ 12ተኛው ደቂቃ መድኖች አቻ ሆነዋል። ጎሉን ከማስቆጠሩ በፊት አደገኛ ሙከራን መሰንዘር የቻለው አማኑኤል ኤርቦ በተጠቀሰው ደቂቃ ብሩንዲያዊው አማካይ አልፍሬድ ኑኩሩንዚዛ የሰጠውን ኳስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ወደ አቻነት አሸጋግሯል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው እና መድኖች በይበልጥ የተሻሉ በነበሩበት አጋማሽ 79ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱ ዳኛ በላይ ታደሠ በሰጡት ቅጣት ምት ከግራ በኩል በተሰጠ ቅጣት ምት ያሬድ በፍጥነት አስጀምሮ የሰጠውን ኳስ ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ከበረከት ሳሙኤል ጀርባ የነበረው አማኑኤል ኤርቦ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ኢትዮጵያ መድን 2ለ1 በሆነ ውጤት ድል ማድረግ ችሏል።
ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል የተደረገው የሸገር ከተማ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ጎል ሳይቆጠርበት 0ለ0 ፍፃሜውን አግኝቷል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች ያገናኘው የዘጠኝ ሰዓት መርሀግብር መቻሎችን አሸናፊ አድርጎ ተቋጭቷል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በመቻል መካከል በተደረገው ጨዋታ 61ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከቀኝ መስመር ከፊቱ ለተገኘው ለጋናዊው ኮሊንስ ኮፊ አቀብሎት አጥቂው በድንቅ አጨራረስ ጎል በማስቆጠር በመጨረሻም ጦሩ 1ለ0 አሸናፊ ሆኗል።

ማምሻው በተደረገው ጨዋታ ደግሞ አዳማ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ አገናኝቶ 1ለ1 ተጠናቋል። አዳማዎች 31ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አካሄድ ከራሳቸው ሜዳ ይዘው የወጡት ኳስ ቢኒያም አይተን ሰጥቶት አቡበከር ሳኒ በጥሩ አጨራረስ ጎል ሲያደርገው ከዕረፍት መልስ ግን 79ኛው ደቂቃ ከያሬድ ታደሰ መነሻዋን ባደረገች ኳስ አብዱሰላም የሱፍ የአቻነት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው ተጠናቋል።
አስተያየት ይስጡ