በሳምንቱ የማሳረጊያ ቀን በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ድሬዳዋ መቐለን 2ለ1 ሲረታ የሀድያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 1ለ1 ተጠናቋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ከፍ በማለት እፎይ ያለበትን ድል መቐለ 70 እንደርታን 2ለ1 በመርታት አስመዝግቧል። ገና 3ኛው ደቂቃ ላይ አጨቃጫቂ በሆነ መልኩ ደስታ ዮሐንስ ጥፋት ሰርተሀል በሚል የተሰጠውን የቅጣት ምት ከሜዳው የቀኝ ክፍል መስመር ላይ አብዱሰላም የሱፍ እጅግ ግሩም ጎል መሐመድ ዛጉዌ መረብ ላይ በማስቀመጥ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡት እና ምስጋና ይግባው እና የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ አብዩ ካሳዬን በተደጋጋሚ ሙከራን ሲሰነዝሩ የታዩት መቐለዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ጎልን ወደ ካዝናቸው ከተዋል።
አብዱሰላም የሱፍ በአሰጋኸኝ ጴጥሮስ ላይ በሰራው ጥፋት በመጀመሪያው አጋማሽ ለድሬዳዋ ራሱ ካስቆጠራት ቦታ ላይ የተገኘችን የቅጣት ምት ደስታ ዮሐንስ አሻምቶ ፍሬዘርን ጨርፎ በግብ ዘቡ አብዩ ስትመለስ ኳሷን ያገኘው ተመስገን ተስፋዬ መረብ ላይ አሳርፏታል። ጎልን ካስተናገዱ በኋላ 52ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ ብርቱካናማዎቹ የድል ግባቸውን አስመዝግበዋል። ሔኖክ ሁሴን በረጅሙ ከራሱ ሜዳ የጣላትን ኳስ አቤል አሰበ ከጨዋታ ውጪ በሚመስል አጋጣሚ ያገኛትን ኳስ ለአብዲሳ ጀማል ሰጥቶት አጥቂው ግብ አድርጓታል።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ ሀድያ ሆሳዕናን ከ አዳማ ከተማ አገናኝቶ የነበረው መርሀግብር 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተፈፅሟል። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም የተለየ የሙከራ አጀብ ያልነበረው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ አቀራረብ የተመለሰ ነበር።
48ኛው ደቂቃ ሀይደር ሸረፋ በጥሩ እይታ ከፍ አድርጎ የሰጠውን ኳስ የሀድያ ሆሳዕናው የመሐል ተከላካይ ቃልአብ ውብሸት ሸውዳው አህመድ ሁሴን እግሩ ስር የገባችን ኳስን እየነዳ በጥልቀት ወደ ሳጥን ገብቶ ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለች ጎልን ማስቆጠር ችሏል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ጫናን ማሳደር የቻሉት ነብሮቹ 61ኛው ደቂቃ ታሪኩ ፀደቀ እዮብ አለማየሁ የሰነጠቀለትን ኳስ ወደ ሳጥን ገፍቶ ገብቶ ክለቡን አቻ አድርጓል።
አስተያየት ይስጡ