ሲዳማ ቡና መሪነቱን የሚያጠናክርበትን ዕድል ሲያመክን መቻል ድል ቀንቶታል።
አዳማ ከተማ 1-3 መቻል
የአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናገደው የመጨረሻ ቀን ብቸኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ ከአማካይ ክፍል በመነሳት ወደ መስመር ለጥጠው መጫወትን መርጠው ከተጋጣሚያቸው አዳማ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት መቻሎች 21ኛው ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ ከእግሩ ያመለጠችውን ኳስ ቻላቸው መንበሩ አግኝቶ ወደ ሳጥን ሲልካት በቸርነት ጉግሳ ተጨርፋ መሐመድ አበራ ጋር ስትደርስ አጥቂው ወደ ጎልነት ለውጦ መቻልን ቀዳሚ አድርጓል።
አዳማ ከተማዎች በሽግግር በመንቀሳቀስ የመጨረሻው ሜዳ ላይ መድረስ ቢችሉም በሚያሳዩት የውሳኔ ልልነት በተቃራኒው በድጋሚ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 45+2 ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ በአግባቡ መሐል ለመሐል የሰጠውን ኳስ መሐመድ አበራ ለበረከት ደስታ በድንቅ እይታ ሰጥቶት ተጫዋቹ መድሀኔ ብርሀኔ እና ሙጂብ ቃሲም እንዲሁም የግብ ዘቡን አላዛር ማርቆስን ጭምር በማለፍ ከመረብ አሳርፏል።
- ማሰታውቂያ -

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ከቆሙበት የቀጠሉት መቻሎች የጎል መጠናቸውን ከፍ ያደረገች ጎልን 63ኛው ደቂቃ ላይ አክለዋል። በረከት ደስታ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ከቁመታሞቹ የአዳማ ተከላካዮች መሐል ዘሎ መሐመድ አበራ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛዋን ጎል በግንባር አስቆጥሯል። ሦስት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ ዘግይተው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ማድረግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የሞከሩት አዳማ ከተማዎች የመቻሉ የግብ ዘብ ከራሱ ሜዳ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ አህመድ ሁሴን ከረጅም ርቀት 85ኛው ደቂቃ ላይ ከሽንፈት ያልታደገች ጎልን ቢያስቆጥርም ጨዋታው በመቻል 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ኢትዮጵያ መድን 1-1 ሲዳማ ቡና
ሲዳማ ቡናዎች የተሻለውን አጀማመር ባደረጉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ጎል የቀረቡት እነርሱ ቢመስልም ጎል ግን ቀድመው አስተናግደዋል። 19ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከግራ ራሱ ያስጀመረውን ኳስ ዳዊት አውላቸው ለወገኔ አቀብሎት አማካይ ወደ ጎል ሲመታ ረመዳን እግሩ ስር የገባችለትን ኳስ መሬት ለመሬት አክርሮ መቶ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። በጎል መቀደማቸው ወደ አቻነት እንዲመጡ የበለጠውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ያስቻላቸው ሲዳማ ቡናዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ በቀለ ከፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ያገኘውን ኳስ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ጨዋታው 1ለ1 ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ሲዳማ ቡናዎች መሪነታቸውን ለማጠናከር ለተጨማሪ ጎሎች በድግግሞሽ ጫናን ሲያሳድሩ መመልከት ብንችልም 90+2 ላይ ሀብታሙ ታደሠን በሁለት ቢጫ ማጣታቸው የአጋማሹ ልዩነት ፈጣሪዋ ክስተት ሆና ጨዋታው በመጨረሻም 1ለ1 ተቋጭቷል።


