ድሬዳዋ ከተማ በመጨረሻ የጭማሪ ደቂቃ ጎል መቐለ 70 እንደርታን 2ለ1 በመርታት ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል።
ድሬዳዋ ከተማ 2-1 መቐለ 70 እንደርታ
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የሳምንቱ የማሳረጊያ መርሀግብር የሆነው የድሬዳዋ እና መቐለ ጨዋታ አስር ሰዓት ሲል በፌድራል ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ መሪነት ጅምሩን ያደረገ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽም በአንፃራዊነት መቐለ 70 እንደርታ መጠነኛ ብልጫን ማሳየት የቻሉበት ነበር።
ከሁለቱም መስመሮች መነሻን ባደረጉ ምንጮች መንቀሳቀስን መርጠው መጫወት የቻሉት መቐለዎች ፍፁም ዓለሙ ካደረጋት እና የግብ ዘቡ ፍሬው ጌታሁን ካመከናት አጋጣሚ በኋላ ከዚሁ እንቅስቀሴ ከግራ መስመር አቅጣጫ ብርሀኑ አዳሙ የሰጠውን በጥሩ አንድ ሁለት የተጫወተው ፍፁም ዓለሙ ሰንጥቆለት በድንቅ አጨራረስ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ መረብ ላይ ያሳረፋት ኳስ ቡድኑን መሪ እንዲሆን አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -


በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ቅያሪን በማድረግ ቅርፅ ይዘው ወደ ሜዳ የተመለሱት ድሬዳዋዎች በፈጣን ሽግግር በተለይ ጀሚል ያዕቆብ እና መሐመድ ኑርናስር በጥልቀት በሚያደርጓቸው ወጥ እንቅስቃሴዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው 49ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ነጋሽ ከቀኝ ወደ ውስጥ የጣለውን ኳስ መሐመድ ኑርናስር በግንባር ገጭቶ ወደ ጎልነት ለውጦ ወደ አቻነት አሸጋግሯል።
በቀጣዮቹም ደቂቃዎች ብልጫዎችን ለመውሰድ ወጥነት በሌለው መልኩ የቀጠለው ጨዋታ ብርሀኑ አዳሙ እና አሸናፊ ሀፍቱ ለመቐለ መሐመድ ኑርናስር ደግሞ ለድሬዳዋ ከተማ ካደረጎቸው አስቆጪ ሙከራዎች በኋላ ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ድሬዳዋ ከተማ የድል ግብን አግኝቷል። 90+3 ላይ ከአብዱሰላም ተነስታ መስዑድ አሾልኮ አቤል ነጋሽ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ የተመለሰች ኳስን ያገኘው ተቀይሮ የገባው አቤል አሰበ የድል ግብ በማድረግ ብርቱካናማዎቹን አሸናፊ አድርጓል።


