የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ ከረፋድ ጀምሮ አካሂዶ አጠናቋል።
ጉባዔው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የመክፈቻ ንግግር ሲጀመር የፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራም ንግግር አድርገዋል።
በመቀጠልም በፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን አማካይነት በተንቀሳቃሽ ምስል የ2017 የበጀት ዓመት አጠቃላይ ሪፖርት ቀርቧል።
በሪፖርቱ በዓመቱ የተከወኑ ጉዳዮች እንዲሁም የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ እንቅስቃሴዎች ቀርበዋል።
- ማሰታውቂያ -

ከሪፖርቱ ቀጥሎም የፋይናንስ ሪፖርት በግዢና ፋይናንስ አስተዳደሩ አቶ ነብዩ ደምሴ የቀረበ ሲሆን በዓመቱ 356,240,896.86 ብር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።
ማርኬቲንግ እና ስፖንሰርሺፕ ፤ ከፊፋ ፣ ከካፍ እና ከሴካፋ ፤ ከሴካፋ የውድድር ማስኬጃ ፤ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ፤ ከፕሪሚየር ሊግ አ.ማ ፤ ከኪራይ ፤ ከተጫዋቾች ቴሴራ ፤ ከምዝገባ እና ዝውውር የክለቦች ውድድር ክፍያ እንዲሁም ሌሎች ያልተገለፁ የገቢ ምንጮች ናቸው ተብሏል።

በወጪ ደረጃ ደግሞ 296,401,320.61 ከአካውንቱ ማውጣቱን በሪፖርቱ ተገልጿል።
ከዚህም መካክል ለወንዶች ብሔራዊ ቡድን የወጣው የ91,294,696.35 ብር ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ተቀምጧል።
በዋነኝነት ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎችን በሀገሩ ማድረግ አለመቻሉ እና በሌሎች ሀገራቶች ለመጫወት መገደዱ ለወጪው እንደምክንያት ቀርቧል።
ለዚህም ከመንግስትም በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኩል 43,887,000.00 ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል።
በተጨማሪም ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን ፤ የጠቅላላ ጉባዔ ማስፈፀሚያ ፤ እርጅና ቅንስናሽ ፤ አስተዳደራዊ ወጪ ፤ ቴክኒክ እና ልማት ፤ የአሰልጣኞች ስልጠና ፤ የሮድ ቱ 2020 ፕሮጀክት እና የዳኞች ልማት በወጪነት የተቀመጡ ናቸው።
በአጠቃላይ ከወጪ ገቢ 59,839,576.25 ትርፍ መገኘቱን ሪፖርቱ አመላክቷል።

ለገቢው ማደግን መንግስት ለብሔራዊ ቡድን ያደረገው ድጋፍ ፤ በታዳጊ ልማት ስራዎች ምክንያት ከፊፋ ተጨማሪ ድጋፍ ማገኘቱ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደ ዋነኛ ምክንያት ቀርበዋል።
ይህም በ2016 የበጀት ዓመት ከተመዘገበው የ27,333,103.52 ኪሳራ በ87,172,679.77 የ2017 ብልጫ አሳይቷል።
ከሪፖርቶቹ በመቀጠልም ከጉባኤው ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች እና ሀሳቦች ቀርበው በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ግብረ መልስ ተሰጥቶባቸዋል።
በተለይም በታዳጊዎች ስልጠና እና በአሰልጣኞች ሰልጠና ዙሪያ ከጉባኤው አባላት ተደጋጋሚ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች ቀርበዋል።
በመቀጠልም በ2018 የበጀት ዓመቱ የፌዴሬሽኑ ዕቅድ ላይ በተመሳሳይ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት ከተደረገ በኋላ በሙሉ ድምፅ ዕቅዱ ፀድቋል።
በመጨረሻም የምርጫ ደንብ ላይ በስድስት አንቀፆች ላይ ማሻሻያ ተደርጎበት ቀርቦ ሀሳቦች ተንሸራሽረውበት በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።


