በበርካታ ደጋፊዎች ፊት የተደረገው የሦስተኛው ሳምንት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ጨዋታዎች በሐይቆቹ እና አፄዎቹ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ሀዋሳ ከተማ 2-1 ወላይታ ድቻ
የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች መካከል የተደረገ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ መልክ የነበረው እንቅስቃሴዎች በይበልጥ የተመለከትንበት ሲሆን 14ኛው ደቂቃ ላይም በፈጣን ሽግግር ለመጫወት ጥረት ያደረጉት የጦና ንቦቹ መሪ መሆን የቻሉበት ነበር። ያሬድ ዳርዛ ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ካርሎስ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ቶሎ ቶሎ የተጋጣሚያቸውን ሦስተኛው የሜዳ ክፍልን መጎብኘትን የጀመሩት ሐይቆቹ 26ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ቢኒያም በላይ ከሽመልስ በቀለ ያገኘውን መሬት ለመሬት ሲያቀብለው ወደ ግራ ኳስን ገፍቶ ሳጥን የገባው ወጣቱ ያሬድ ብሩክ በድንቅ አጨራረስ ቢኒያም ገነቱ መረብ አሳርፎ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ወደ አቻነት መምጣታቸው በራስ መተማመናቸውን ከፍ ያደረገላቸው ሀዋሳ ከተማዎች 37ኛው ደቂቃ ከእጅ ውርወራ የአብስራ ደግፌ የሰጠውን ኳስ ሳጥን ጠርዝ ሆኖ ያገኘው ያሬድ ብሩክ እጅግ አስደናቂ ጎልን በድጋሚ ቢኒያም ገነቱ የኋላ መረቡ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሸጋግሯል።
ከዕረፍት ሲመለስ የቀጠለው እና በይበልጥ የሚቆራረጡ ኳሶች የተበራከቱበት አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ያስቆጠሯቸውን ጎሎች በማስጠበቅ በጥቂቱ ግን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ወላይታ ድቻ ግን የተጫዋቾች ቅያሪን በማድረግ ጫናዎች በሚያሳድሩ ረጃጅም ኳሶቻቸው ብልጫውን መያዝ ቢችሉም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2ለ1 የበላይነት ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -

ፋሲል ከነማ 1-0 ሲዳማ ቡና
ሌላኛው ምሽቱን በርካታ ደጋፊዎች የታደሙበት የፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ የቡናማዎች የኳስ ንክኪ ብልጫ የአፄዎቹ ደግሞ የጥንቃቄ አጨዋወትን በሙሉ የጨዋታ ደቂቃው ያስዋልንበት ነበር ማለት ይቻላል። ከጅምሩ ከመስመር መነሳትን መርጠው የበላይነትን በሜዳቸው ሲያሳዩ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች 14ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል ስህተት ጎልን ለማስተናገድ ተገደዋል። ያሬድ ባዬ ከአስቻለው ሙሴ ያገኘውን ኳስ ወደ ኋላ ለዮሴፍ ዮሐንስ ሲያቀብለው ከጀርባው የነበረው በረከት ግዛው በጥሩ አጨራረስ በሦስት ጨዋታ ሦስተኛ ጎሉን በማስቆጠር ፋሲልን መሪ በማድረግ አጋማሹ ተገባዷል።
ከዕረፍት በፊትም የበላይ የነበሩት እና በሁለተኛውም አጋማሽ ከቆሙበት የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ ቢያንስ ወደ አቻነት ለመምጣት ከየትኛውም አቅጣጫ ሳጥን በሚጣሉ የዐየር ላይ እና የመሬት መሬት ማቀበሎችን ቶሎ ቶሎ ቢያሳዩንም ከነበራቸው ጥድፊያዎች አኳያ የግብ ዘቡን ሞይስ ፓዎቴን ድንቅ ብቃት ተገዳድረው ጎሉን ማስቆጠር ግን አልቻሉም። በመከላከል ይጠመዱ እንጂ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ጎል ሊሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ያገኙ የነበሩት አፄዎቹ በመጨረሻም ተሳከሰቶላቸው 1ለ0 አሸናፊ ሆነው ወጥተዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተደጋጋሚ ከአራተኛው ዳኛው አዳነ ወርቁ ጋር በጨዋታ እና ከጨዋታ በኋላ ጭቅጭቅ ሲፈጥር የነበረው ደግፌ ዓለሙ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።


