የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ የአዲስ አበባ ስታድየም ሁለት ጨዋታዎችን አሰትናግዷል።
ከቀን 7:00 ጀምሮ የተደረገው የኢትዮጵያ መድን እና አዳማ ከተማ ተጠባቂ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም በኩል አስቀድሞ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶች ተደርገዋል።
ምንም እንኳን በሁለቱም በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶች ቢኖሩም በግብ ሙከራዎችን የታጀቡ አልነበሩም።
- ማሰታውቂያ -

16ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ መድን በኩል ረመዳን የሱፍ በቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢልከውም የግቡ ቋሚ መልሶበታል።
በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ 38ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም አይተን ከአህመድ ሁሴን የተቀበለውን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ከግብ ሙከራዎች እና ሽኩቻዎች ጋር ባስመለከተን የሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ታይቷል።
በ48ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆጤሳ በሳጥኑ የቅርብ ርቀት ያገኘውን የቅጣት ምት ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቀዳሚውን ግብ ለማድረግ የሚደረጉት ጥረቶች በቀላሉ የተጋጣሚ ሳጥን ገብተው የግብ ዕድል ለመፍጠር አልቻሉም።
በዚህም በተለይም ከሳጥን ውጪ የሚደረጉ መከራዎች በተደጋጋሚ በጨዋታው ተስተውለዋል።
በቀጣይም በ56ኛው እና 60ኛው ደቂቃዎች ላይ ዳዋ ሆጤሳ እና አህመድ ሁሴን ከሳጥን ውጪ ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል ደግሞ ወገኔ ገዛኸኝ ሁለት ጠንከር ያሉ የግብ ሙከራዎችን ከሳጥን ውጪ ቢያደረግም በግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ተይዞበታል።

በጨዋታው የአዳማ ከተማው አምበል ሀይደር ሸረፋ የቀድሞ ቡድኑን በገጠመበት ጨዋታ በበረከት ካሌብ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በመጨረሻም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት የተጠናቀቀ የመጀመሪያው ሳምንት ብቸኛ ጨዋታ ሆኗል።
ከ10:00 ጀምሮ የተደረገው የባህርዳር ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ የ3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው ባህርዳር ከተማዎች መሪ ለመሆን የፈጀባቸው ሰባት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ናቸው።
በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ክንዱ ባየልኝ በግንባር በመግጨት ከመረብ ላይ አሳርፎታል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል በፈጣን የጨዋታ ሒደቶች ግቦችን ለማስቆጠር ጥረቶች ተደርገዋል።
በነብሮቹ በኩል ተመስገን ብርሀኑ እና ሔኖክ አርፊቹ ያደረጓቸው እና በፔፔ ሰይዶ ተሞክረው የተያዙት ኳሶቹ በቡድኑ በኩል የተደረጉ ኢላማቸውን የጠበቁ የመጀመሪያው አጋማሽ ሙከራ ናቸው።
በባህርዳር ከተማ በኩልም በተደጋጋሚ ወደ ሀድያ ሆሳዕና ሳጥን መድረስ ቢችሉም ግብ ጠባቂውን የፈተነ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
በሁለተኛው አጋማሽ ባህርዳር ከተማዎች ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠር ከሁለት ደቂቃ ያነሰ ጊዜ ነበር ያስፈለጋቸው።

የቡድኑ አዲስ ፈራሚ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከወንድወሰን በለጠ ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ተልኮ የሀድያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ያሬድ በቀለ በቀላሉ ለመቆጣጠር ሳይችል በመቅረቱ ኳሱን ያገኘው አማኑኤል ኳስ እና መረበንን አገናኝቷል።
የ2 ለ 0 መመራትን ለመቀልበስ የተለያዩ ቅያሪዎችን በማድረግ ጨዋታውን የቀጠሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በጫላ ተሺታ አማካይነት ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል።
ባህርዳር ከተማ የሶስተኛ ሀድያ ሆሳዕናዎች ደግሞ የአቻነት ግብ ፍለጋን ሲያደርጉት ከነበረው ጥረት ባለፈ ከባባድ ጥፋቶችም በጨዋታው ተስተውለዋል።

በተለይም ኤልያስ አህመድ በክንዱ ባየልኝ ላይ የሰራው አደገኛ ጥፋት ተጫዋቹን የቀጥታ ቀይ ካርድ ሰለባ አድርጎታል።
የውጤትም የተጫዋች ቁጥርም ብልጫ የተወሰደባቸው ነብሮቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግብ ለማግኘት ብልጫን ወስደው ቢጥሩም በተቃራኒው ግብ አስተናግደዋል።
ተቀይሮ የገባው ሴዝ ኦሴ በ78ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ከመረብ ላይ አርፏል።
በመጨረሻም ባህርዳር ከተማ በ3 ለ 1 ውጤት በጨዋታው አሸናፊ ሆኗል።


