በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተደረጉ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ፋሲል እና ንግድ ባንክ ነጥብ ሲጋሩ መቻሎች በጭማሪ ደቂቃ ጎል ወሳኝ ድል አግኝቷል።
ፋሲል ከነማ 1-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሊጉ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሁለቱን በአዲስ አሰልጣኞች የሚመሩ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ መልክ የነበረው ቢመስልም አፄዎቹ ግን በአንፃራዊነት ፈጣን አጀማመር ባደረጉበት ሂደት 8ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ጎል አስቆጥረዋል። በረከት ግዛው ከራሱ እግር የተነሳች ኳስን ከዳግም አወቀ መልሶ ተቀብሎ ወደ ጎልነት በመለወጥ ቡድኑን መሪ ቢያደርግም መሪነታቸው የቆየው ግን ለአራት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 12ኛው ደቂቃ ላይ የማዕዘን ምትን ያገኙት ንግድ ባንኮች አዲስ ግደይ አሻምቶ ዘላለም አበበ በግንባር ገጭቶ ከመረብ አዋህዶ ጨዋታውን ወደ1ለ1 ለውጧል። ጨዋታው ሊገባደድ ሲቃረብ አፄዎቹ በቃልኪዳን ዘላለም አማካኝነት ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች ቢያገኙም የግብ ዘቡ ፓላክ ቾል በአጋማሹ ጎል እንዳይሆኑ አግዷቸዋል።
ከዕረፍት መልስ የቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታው በእንቅስቃሴም ይሁን በጎል ሙከራዎች እምብዛም መታጀብ ያልቻለ ሲሆን አብዛኛዎቹም እንቅስቃሴዎች ሐይል የቀላቀለበት ነበር ማለት ይቻላል በዚህም የተነሳ ሀብታሙ ተከስተ እና ዘላለም አበበ ኳስን ለመሻማት ጥረት ሲያደርጉ በተፈጠረ ግጭት ካስተናገዱት ጠንከር ያለ ጉዳት ውጪ ተጨማሪ መልኮችን ማጀብ ሳይችል ጨዋታው 1ለ1 መቋጨት ችሏል።
- ማሰታውቂያ -

መቻል 1-0 ወላይታ ድቻ
አመሻሹን በጀመረው የመቻል እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች በሁሉም ረገድ መቻል ብልጫውን ቢይዙም በመጀመሪያው አጋማሽ ብቸኛ ሙከራን ያደረጉት የጦና ንቦቹ ሲሆኑ ቴዎድሮስ ታፈሠ ከማዕዘን አሻምቶ አዘሪያስ በግንባር ገጭቶ የግብ ዘቡ አሊዮንዚ ናፊያን የመከተበት ተጠቃሿ ሙከራ ስትሆን ከዕረፍት መልስ ግን ወላይታ ድቻ በመከላከል መቻሎች በበኩላቸው ሙሉ በሙሉ ጨዋታውን መቆጣጠር ቢችሉም ጨዋታው በጎል ሙከራዎች መድመቅ የተሳነው ሆኖ ረጅሙን ደቂቃ ቆይቷል። የተጫዋቾች ቅያሪን በማድረግ አንዳች ነገርን ከጨዋታዉ የፈለጉ የሚመስሉት የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረቱ ቡድን ተሳክቶላቸው ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው 90+3 ላይ ተቀይሮ የገባው ናይጄሪያዊው አማካይ መናፍ ኢሞሮ በግምት ከሰላሳ ሜትር ርቀት የግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ የቦታ አያያዝ ስህተት ታክሎ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በመጨረሻም በመቻል 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


