በሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ተጠባቂ በነበረው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ዕጅግ በርካታ ደጋፊዎች አጅበውት በተጀመረው ጨዋታው በሁለቱም በኩል አስደንጋጭ የግብ ሙከራዎች ተደርገው ነበር።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ቀዳሚው ሙከራ ሲደረግ አቡበከር አዳሙ ከረጅም ርቀት ከቆመ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሐንስ ኳሱን አውጥቶታል።
ከዚህ ሙከራ ሰከንዶች በኋላ አቤል ያለው በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ዳንላድ ኢብራሂም ተቆጣጥሮታል።
- ማሰታውቂያ -

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተለይም በመስመሮች በኩል የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አልነበረም።
በተለይም የፋሲል ተካልኙ ቡድን የቡናማዎቹን የመስመር እንቅስቃሴ ለመገደብ በማሰብ በሚመስል መልኩ በሲቲ ካፕ ላይ የተጠቀማቸውን የመስመር ተከላካዮች በመለወጥ ቶሎሳ ንጉሴ እና ጳውሎስ ከንቲባን በጨዋታው ተጠቅሟል።
ከመስመር እንቅስቃሴዎች ባለፈም የአሰልጣኝ አብይ ካሳሁን ቡድን ከቆሙ ኳሶችም ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ስኬታማ አልሆኑም።
በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ተጋጣሚ ግብ በመድረስ ብልጫ የተወሰደባቸው ፈረሰኞቹ አቤል ያለውን ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ለማድረስ ሞክረዋል።
ከሜዳ ውጪ በደጋፊዎች ዘንድ ያለውን ድባብ ያልደገመው የሜዳ ላይ እንቅሰቃሴው ከመጀመሪያ ደቂቃዎች ሙከራ ባለፈ ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ ሙከራ ሳያስመለከት አጋማሹ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጨዋታውን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡናን የግብ ክልል መፈተሽ ችለዋል።

ጨዋታው 52ኛው ደቂቃ ላይ ላይ ሲደርስ ግን የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ዳንላድ ኢብራሂም በአቤል ያለው ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
የዳንላድን የቀይ ካርድ በተመለከተ ከጨዋታዉ በኋላ አሰልጣኝ አቢይም ሆነ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የጨዋታውን እንቅስቃሴ የቀየረ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቁጥር ብልጫው በኋልም ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ66ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል።
አዲሱ አቱላ ከቢንያም ፍቅሬ የደረሰውን ኳስ ነፃ ለነበረው አቤል ያለው አቀብሎት የፈረሰኞቹ አምበል ያገኘውን ኳስ መረብ ላይ አሳርፏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ በይበልጥ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደጋግመው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር።

ነገር ግን በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ላይ የሚደርሱት ያልተረጋጉ ኳሶች እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ለተጋጣሚያቸው ተጫዋቾች ክፍተት አለመፍጠራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ተመስገን ዮሐንሰንን የፈተነ የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል።
በ76ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአጥቂው ሻባን ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቷል በሚል ቅሬታቸውን ቢገልፁም ሁነቱ የዕለቱን ዋና ዳኛ ያሳመናቸው አልሆነም።
በይበልጥ ኳስ በያዙ ሰዓት ተረጋግተው ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ፈረሰኞቹ በአቤል ያለው ፣ ቢንያም ፍቅሬ እና አፈወርቅ ሀይሉ አማካይነት ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።
በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ በአቤል ያለው ብቸኛ ግብ በደርቢው ከስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ማሸነፍ ችሏል።


