በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተደረጉ ሁለት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ወልዋሎን ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ድሬዳዋን በመርታት ዓመቱን በድል ጀምረዋል።
ወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርስቲ 1-4 ሲዳማ ቡና
በቅርቡ በድንገኛ አደጋ ህይወቱ ላለፈው ፌድራል ረዳት ዳኛ ደረጀ አመራ ለህሊና ፀሎት በማድረግ የጀመረው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የተሻሉ ቢመስሉም በሽግግር ቶሎ ቶሎ የተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ለመድረስ ብዙም ያልከበዳቸው ወልዋሎዎች ብሩክ እንዳለ ያለቀለትን ኳስ ከሜዳው የግራ አቅጣጫ አግኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረበት ቅፅበት ቀዳሚዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች።
ሲዳማ ቡናዎች በሁለቱም ኮሪደሮች ደጋግመው ለማጥቃት ቢዳዱም የመጨረሻው የሜዳ ክፍል አጠቃቀማቸው ስልነት ባለመሆኑ በተቃራኒው ጎልን አስተናግደዋል። 35ኛው ደቂቃ አማካዩ ብሩክ እንዳለ በረጅሙ ወደ ግራ የጣለውን ኳስ ሠመረ ሀፍታይ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ለውጧት ቡድኑን መሪ አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -


ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው የመለሱት ሲዳማ ቡናዎች በፍፁም የበላይነት ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። ከፍ ባለ የሽግግር እንቅስቃሴ የተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ የዋሉት የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ልጆች 56ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ሙሴ ከግራ ያሻማውን ኳስ በሊጉ ባለፈውም አመት በኤሌክትሪክ ቆይታው በራሱ ላይ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ጌታሁን ባፋ በራሱ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፏት ጨዋታው ወደ አቻ ውጤት ተለውጧል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ ይበልጥ በመከላከሉ ፍፁም ደካሞች የነበሩት ቢጫዎቹ ከአምስት ደቂቃዎ መልስ አበባየሁ ሀጂሶ ከመረብ ባዋሀዳት ጎል ወደ 2ለ1 ሊመሩ ተገደዋል።
በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው ፋታ በማይሰጠው እንቅስቃሴያቸው የቀጠሉት ቡናማዎቹ 65ኛው ደቂቃ አስቻለው ሙሴ ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር የሲዳማን የጎል መጠን ከፍ ሲያደርግ 75ኛው ደቂቃ ከተመስገን በጅሮንድ የተሻማለትን ኳስ ተመስገን መንገሻ በግንባር ገጭቶ ጨዋታው ወደ 4ለ1 ተለውጧል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ የወልዋሎው አማካይ ብሩክ እንዳለ በሰራው አደገኛ ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ከተወገደ በኋላ ጨዋታው መጠናቀቅ ችሏል።
ድሬዳዋ ከተማ 0-2 ሀዋሳ ከተማ
ምሽቱን ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው እና በፌድራል ዋና ዳኛ ሀይማኖት አዳነ የተመራው የምሽቱ ጨዋታ ተመጣጣኝ እና ሳቢ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ ያስመለከተን ነበር። በይበልጥ ከመስመር መነሳት መርጠው ለመጫወት ሙከራዎችን ሲያደርጉ የሚስተዋሉት ሀይቆቹ በሽመልስ በቀለ ካደረጓት ሙከራ መልስ በሁለተኛው አጋጣሚ ከጎል ጋር ተገናኝተዋል። 10ኛው ደቂቃ ቸርነት አውሽ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞ የገባትን ኳስ ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

መሐመድ ኑርናስር በተሰለፈበት የግራው አቅጣጫ ፈጥነው ሳጥን በመግባት ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያልተለያቸው ድሬዳዋ ከተማዎች የሀዋሳው ተከላካይ ፍቃደስላሴ ደሳለኝ መሐመድ ኑርናስር ላይ ሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መሐመድ መቶ የግብ ዘቡ ሰይድ ሀብታሙ መልሶበታል። ሀዋሳዎች በአብነት ደምሴ ድሬዳዋዎች በመሐመድ ኑርናስር ሙከራን ቢያደርጉም አጋማሹ በ1ለ0 ውጤት ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ ተመሳሳይ በሆኑ የሁለቱም ቡድኖች የጨዋታ አቀራረብ በቀጠለው ጨዋታ ሀዋሳዎች ከጎል ጋር ለመገናኘት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ከተጋጣሚያቸው አንፃር የሰላ ነበር። ጌታነህ ከበደ በአንድ ለአንድ ግንኙነት የግብ ዘቡ ፍሬው ጌታሁን ከማከነበት በኋላ ደቂቃው 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሽመልስ በቀለ ጣጣውን የጨረሰ ኳስን ሲያቀብለው ጌታነህ ከበደ ልምዱን ተጠቅሞ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በመጨረሻም በ2ለ0 ውጤት ተጠናቋል።


