እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1 ሲረታ ባህርዳር ከተማ 2ለ1 በሆነ ውጤት አዳማ ከተማን አሸንፏል።

ባህርዳር ከተማ 2-1 አዳማ ከተማ
ዘጠኝ ሰዓት ሲል ባህርዳር ከተማን ከአዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ጨዋታ ጎል የተቆጠረው 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ባህርዳሮች ደግሞ ቀዳሚዎቹ ናቸው። መሳይ አገኘሁ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ብሩክ ሰሙ በግንባር ገጭቶ ወደ ጎልነት ለውጧት የጣናውን ሞገድ ቀዳሚ አድርጓል። 26ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን አጋጣሚ አግኝተዋል። ግርማ ዲሳሳ በሳጥኑ ውስጥ ቢኒያም አይተን ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቢኒያም ወደ ግብነት ለውጧታል።

በተሻለ የመጫወት ፍላጎት በንፅፅር ብልጫውን የወሰዱት እና በድግግሞሽ ማጥቃት ክፍሉ ላይ ይገኙ የነበሩት ባህርዳሮች ከዕረፍት መልስ 63ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ የሆኑበትን ጎል ወደ ካዝናቸው ከተዋል። ከሔኖክ ይበልጣል ተነስታ ግርማ ዲሳሳ ወደ ጎልነት መቶ መናፍ አወልን ገጭታ ስትመለስ ከሳጥኑ ጫፍ ኳሷን ያገኘው አንተነህ ተፈራ በግራ እግሩ የናትናኤል ተፈራ መረብ ላይ አስቀምጧት ጨዋታው በባህርዳር ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ሲዳማ ቡና 1-3 መቻል
ሲዳማ ቡናዎች ጥሩ ለመንቀሳቀስ ጥረት ባደረጉበት የመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ጎልን ለማስቆጠር 28 ደቂቃዎችን ጠብቀዋል። አቤል ያለው ከቀኝ የሜዳው ክፍል ያደገኘውን ኳስ ከግቡ የቀን ቋሚ ጫፍ ሙከራ አድርጎ የግብ ዘቡ አሊዮንዚ ናፊያን ሲመልሳት ጥሩ ቦታ ሆኖ ኳሷን ያገኘው ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

እጅግ ከባድ በሆነ ዝናብ ታጅቦ በቀጠለው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ለቅብብል አመቺ ባልሆነ ሜዳ ላይ መቻሎች ቀስ በቀስ ጨዋታውን በደንብ በመቆጣጠር የበላይ ወደ መሆን መጥተው የአቻነት ጎል አግኝተዋል። ሁለት ያለቀላቸውን ዕድሎች አምክነው የነበሩት ጦረኞቹ 41ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ጋናዊው አጥቂ ኮሊንስ ኮፊ ወደ ግብ ያሻገረው ኳስ የያሬድ ባዬን በጉዳት ተቀይሮ መውጣት ተከትሎ መከላከሉ የሳሳባቸው ሲዳማ ቡናዎች ቸርነት ጉግሳ የገኘችውን ኳስ መረቡ ላይ አሳርፎ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በተሻለ መነቃቃት የተመለሱት መቻሎች መሪ ወደ መሆን መጥተዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ኮሊስ ኮፊ ያሻማትን ኳስ ተጨርፋ ያገኘው ግሩም ሀጎስ በግራ እግሩ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑ 2ለ1 አድርጓል። መደበኛው ደቂቃው ሊጠናቀቅ 89ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በረከት ደስታ ራሱ በማጥቃት ያስጀመረውን ኳስ በኋላም ቸርነት ጉግሳ ወደኋላ አቀብሎት በረከት ደስታ ከሳጥን ውጪ እጅግ አስገራሚ ጎሉን መስፍን ሙዜ መረብ ላይ በማሳረፍ መቻል 3ለ1 በሆነ ውጤት የሊጉን መሪ ረቷል።
አስተያየት ይስጡ