የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታዎች ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ተደርገው በተመሳሳይ የ3 ለ 1 ውጤት ተጠናቀዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ በነበረው ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን 3 ለ 1 በማሸነፍ ከ53 ቀናት አልያም ስድስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በኋላ አሸንፏል።
በጨዋታው 30ኛ ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ ሀድያ ሆሳዕናን መሪ ሲያደርግ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ዘላለም አባተ ያስቆጠረው ግብ ወላይታ ድቻን አቻ አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽ በ71ኛው እና 80ኛው ደቂቃዎች ላይ በየነ ባንጃ እና ደስታ ዋሚሾ ያስቆጠሯቸው ግቦች ሀድያ ሆሳዕናን አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል።
- ማሰታውቂያ -

ውጤቱንም ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 37 በማድረስ በጊዜያዊነት ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ወላይታ ድቻ በበኩሉ በ37 ነጥቦች ወደ 5ኛ ደረጃ ተንሸራቷል።
በ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀድያ ሆሳዕና ከፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻ ደግሞ ከስሁል ሽረ ይጫወታሉ።
ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ከ76 ቀናት በፊት ወላይታ ድቻን ከረታ በኋላ ከድል የራቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሶስት ነጥብ ጋር ተገናኝቷል።
በዓመቱ አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈውን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ቢንያም ፍቅሩ ጨዋታው በጀመረ 47ኛው ሰከንድ ላይ ባስቆጠረው ግብ ፈረሰኞቹ ለ67 ደቂቃዎች መምራት ችለው ነበር።
በ68ኛው ደቂቃ ላይ ቡልቻ ሹራ በቀድሞ ክለቡ ላይ ያስቆጠረው ግብ ወልዋሎ አዲግራትን አቻ አድርጎ ነበር።
አብዱ ሳሚዮ በ81ኛው ቢንያም ፍቅሩ ደግሞ በድጋሚ በ88ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቶታል።
ውጤቱንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 34 በማድረስ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወልዋሎ አዲግራት በ11 ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።
በ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ መቀሌ 70 እንደርታን ወልዋሎ አዲግራት ደግሞ አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።


