የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ከረፋድ እስከ ምሽት ድረስ ተደርገዋል።
ከረፋድ 3:30 ጀምሮ በተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፏል።
የሳይመን ፒተር የ21ኛ ደቂቃ ግብ የአምናውን ሻምፒዮን አሸናፊ ለማድረግ በቂ ነበር።
ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ተመስገን ዮሐንስ ከግቡ ሲያርቅ ያገኘው ጋናዊው አጥቂ በቀጥታ በመምታት በ21ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነው በመጫወት የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
በሊጉ በስኬታማነት ቀዳሚ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዘመኑ ስምንተኛ ሽንፈቱ ሲሆን ፤ ከድል ከተራራቀ ደግሞ ሰባተኛ ተከታታይ ጨዋታው ሆኖ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 35 ማድረሱን ተከትሎ በጊዜያዊነት ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በ31 ነጥቦች ወደ 11ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ ሲዳማ ቡና ባህርዳር ከተማን በፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል።
በ24ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ሙሴ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ተጨራርፎ ያገኘው ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን አክርሮ በመምታት አስቆጥሮታል።
አስር ቁጥር ለባሹ ባሳለፍነው ሳምንትም ቡድኑ ስሁል ሽረን ሲረታ የማሸነፊያውን ብቸኛ ግብ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።
ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 32 አድርሶ በጊዜያዊነት ደረጃውን ከ12ኛ ወደ 9ኛ አሻሽሏል።
ባህርዳር ከተማ በበኩሉ ከኢትዮጵያ መድን ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት የሚያጠብበትን ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል።
እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች ስታድየም ተገኝተው በተከታተሉት እና ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፏል።
ለሀዋሳ ከተማ ኤርትራዊው ዓሊ ሱሌማን በ47ኛው ደቂቃ ላይ በረጅም የደረሰውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በቮሊ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሯል።
ሀዋሳ ከተማ ያለውን ነጥብ 24 ቢያደርስም አሁንም ከወራጅ ቀጠናው መላቀቅ(15ኛ) አልቻለም።
ከሰባት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በኋላ የተሸነፈው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ነጥቡን 40 አድርሶ ከኢትዮጵያ መድን ያለውን ልዩነት ወደ 5 የሚያጠብበትን ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል።
ወላይታ ድቻ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ያስተናገደበት ጨዋታ ሲሆን ግብ አስቆጣሪው ዓሊ ሱሌማን በበኩሉ 10ኛ የውድድር ዓመት ግቡ ሆኗል።
የሊጉ መርሐግብር በነገው ዕለትም ሲቀጥል ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ እንዲሁም መቻል ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ።


