ከወራት በፊት ወደ አሜሪካ ያቀናችው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አምበል ሎዛ አበራ በቨርጂኒያ ማራውደርስ ያለፉትን ጊዜያት ቆይታ ማድረጓ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ አዲስ ክለብ መቀላቀሏ ይፋ ሆኗል።
ሎዛ አበራ የተቀላለችው የዲሲ ፓወር ክለብ በቅርብ የመሰረተ ሲሆን ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካሔድ ላይ ባለው የአሜሪካ የሴቶች ሱፐር ሊግ ወድድር ተሳታፊ ከሆኑት ስምንት ክለቦች አንዱ ነው።
የአሜሪካ የሴቶች ሱፐር ሊግ ከታዋቂው የናሽናል ሶከር የሴቶች ሊግ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ የሊግ ወድድር ሆኖ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ክለቡ የሎዛን መፈረም ይፋ ባደረገበት መግለጫውም በአሜሪካ የመጀመሪያው የሊግ እርከን ለመጫወት የቻለች ቀዳሚዋ ኢትዮጵያዊት ተጫዋች ናት ብሏታል።
- ማሰታውቂያ -
የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፈረንሳያዊው ፍሬድሪክ ብሪላንት ሎዛን በማስፈረማቸው መደሰታቸውን በመግለፅ በወጥነት ግቦችን ማስቆጠር የምትችል ተጫዋች መሆኗን ገልፀዋል።
አክለውም ለቡድኑ የማጥቃት ሐይል ትልቅ አቅም እንደምትሆንም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የክለቡ ፕሬዚዳንት ጆርዳን ስቱዋርት በበኩላቸው እጅግ የተለየ ብቃት ያላት ተጫዋች ናት ፤ የሀገሯን ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት በመምራት ከአፍሪካ ምርጥ ተጫዋቾች አንዷ መሆኗን አሳይታለች ብለዋል።
በተጨማሪም የዲሲ ፓወር ክለብ መቀመጫ በሆነው ዋሽንግተን ዲሲ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ያሉ በመሆናቸው የሎዛ ክለቡን መቀላቀል በርካታ ኢትዮጵያዊያን ደጋፊዎች ለማግኘት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።
የሉሲዎቹ አምበል የሆነችው ሎዛ አበራ በዲሲ ፓወር ከጋናዊቷ ጄኒፈር ኩድጆ እና ካሜርናዊቷ ግሬስ ጎክ በመቀጠል ሶስተኛዋ አፍሪካዊት ተጫዋች ሆናለች።
ክለቡ ሎዛ ለምን ያህል ዓመት እንደፈረመች እና የደመወዝ እና ጥቅማጥቅሞች ስምምነቶችን በመግለጫው አላካተተም።
ሎዛ አበራ በቀደመ ክለቧ ቨርጂንያ ማራውደርስ በነበራት ቆይታ በዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ በመጀመሪያ አሰላለፍ በመካተት የጀመረች ሲሆን ስምንት ያህል ግቦችንም አስቆጥራለች።
ዲሲ ፓወር በመጀመሪያ ሁለት የሊግ ጨዋታዎቹ በአንዱ ነጥብ ሲጋራ በአንዱ ሸንፈትን ያስተናገደ ሲሆን የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታውን በመጪው ቅዳሜ ምሽት 3:00 ጀምሮ ከሜዳው ውጪ ከዳላስ ትሪኒቲ ጋር ያደርጋል።