“ህልሜ የተሳካበት ቀን ነው”
“ሻምፒዮን ስለመሆን ነው የማስበው”
“የኢትዮጵያን ህዝብም ዲሲ ፓወርንም ማኩራት ነው የምፈልገው”
ሎዛ አበራ ( ዲሲ ፓወር)
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አምበል የሆነችው ሎዛ አበራ የአሜሪካ ሴቶች ሱፐር ሊግ ተሳታፊ የሆነውን ዲሲ ፓወርን መቀላቀሏን ቀደም ብለን መዘገባችን ይታወቃል።
ተጫዋቿ ፊርማዋን ካኖረች በኋላም በጋዜጣው መግለጫ ላይ ያካፈለችውን ሀሳብ ለዝውውሯ መሳካት ትልቁን ድርሻ የወሰደው የፊፋ ማች ኤጀንት እና አሰልጣኝ መዝሙረዳዊት መኩሪያ በማህበራዊ ትስስር ገፁ አጋርቷል።
በጣም ደስ ብሎኛል ስትል ንግግሯን የጀመረችው ሎዛ አበራ ህልሜ የተሳካበት ቀን ነው ብላለች። አክላም እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎች ስለመሻገሯ ተናግራለች።
“እዚህ ቦታ ለመቀመጥ በእግርኳስ ህይወቴ ውስጥ ብዙ ታግያለሁኝ። ዛሬ ደግሞ ህልሜ እውን ስለሆነ በጣም ደስ ብሎኛል።”
በቨርጂኒያ ማራውደርስ አስቀድማ ቆይታ ያደረገችው ሎዛ በክለቡ በነበራት ቆይታ በ11 ጨዋታዎች ላይ አስር ግቦችን አስቆጥራ ሰባት ደግሞ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችታ ማቀበሏን አስታውሳለች።
በዚህም በዲሲ ፓወር ክለብ ሰዎች አይን ውስጥ መግባቷን እና በተሰጣትም የሙከራ ጊዜ በሚገባ አቅሟን በማሳየቷ በክለቡ በቋሚነት ፊርማዋን ለማኖር እንዳገዛት ገልፃለች።
የዲሲ ፓወር እግርኳስ ክለብ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ ያልቻለ ሲሆን የሎዛ ቡድኑም መቀላቀል የአጥቂ ክፍሉን እንደሚያጠናክረው አሰልጣኙ የሰጡትን አስተያየት አቅርበናል።
ሎዛም በዚህ ዓመት ከቡድኑ ጋር ዋንጫ ስለማሸነፍ እንደምታስብ በመግለጫው ላይ ተናግራለች።
“ከዲሲ ፓወር እግር ኳስ ክለብ ጋር በዘንድሮው ዓመት ትልቅ ስራ ሰርተን በሊጉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እና ሻምፒዮን ለመሆን ነው አንድ ላይ የማስበው።”
“ባለኝ አቅም ሁሉ ለቡድኑ የተሻለ ነገር ሰርቼ የኢትዮጵያን ህዝብም ዲሲ ፓወርንም ማኩራት ነው የምፈልገው።”
በክለቡ መቀመጫ በሆነው የDMV አካባቢ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩ መሆኑን ተከትሎም ለክለቡ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር በመጥቀስ ስታድየም በመገኘት ክለቡን እንዲደግፉ እና እሷንም እንዲያበረታቷት ጥሪ አቅርባለች።
“የኢትዮጵያ ህዝብ ኳስ የሚወድ ህዝብ ነው። ዲሲ ፓወር DMV አካባቢ በመቋቋሙ ደግሞ ብዙ ደጋፊዎች የዲሲ ፓወር ቤተሰብ እንደሚሆኑ አምናለሁ።”
“ይህ ዜና ይፋ ከሆነ በኋላ ብዙ ደጋፊዎች እንደምናገኝ እና ብዙዎች የዲሲ ፓወር ቤተሰብ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነኝ።”
ሎዛ አበራ አክላም ቡድኑ በመጪው መስከረም 2/2017 በሜዳው ኦዲ ፊልድ በሚያደርገው የዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታም እዛ አካባቢ ያለ ኢትዮጵያ ተገኝቶ ክለቡን እንዲደግፍ እና ከኔም ጎን እንዲሆን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ብላለች።
ሎዛ እዚህ ለመድረሷ ያገዟትን ግለሰቦች ስም በመጥቀስ ጭምርም በመግለጫው ላይ አመስግናለች።