የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ የቀረበበትን ቅሬታ ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በክለቡ ላይ ውሳኔ አሳልፏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐግብር ከኢትዮጵያ ቡና 2 – 2 ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ በጨዋታው በነበረው በየዳኝነት ውሳኔዎች ላይ ደስተኛ አለመሆኑን በማመላከት ቅሬታ አቅርቧል።
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው የቅሬታ ደብዳቤ ላይም የውድድሮች አመራር ዳኝነት የተወሰኑ ክለቦችን ወደ ክብር ኮርቻ ለማስቀመጥ በሚመስል መልኩ በውድድሮች ላይ ከሚመደቡ አንዳንድ ዳኞች መዋለ ንዋይ በመመደብ የአንድ ድርጅት ተወካይ ቡድን ድካምና ልፋት ውጤት የሚቀይሩ አነጋጋሪ የሆኑ ውሳኔ ሲወስኑ የታዩ በመሆኑ ለተፈፀመው የዳኝነት መዛባትም ሆነ በቀጣይ ጨዋታዎች ስለሚኖረው ፍታዊ ዳኝነት ዋስትና እንዲሰጠን በማለት ማቅረቡን የፌዴሬሽኑ መግለጫ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ደግሞ የቀረበው አቤቱታ ከተመለከተ በኋላ ግንቦት 04 ቀን 2016 ዓ.ም ባቀረበው አቤቱታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር በዳኞች ላይ የስም ማጥፋት ተግባር የፈፀመ በመሆኑ ጉዳዩ ተጣርቶ ተገቢው ውሳኔ ይሰጥልኝ በማለት ለዲስኘሊን ኮሚቴ አቅርቧል፡፡
- ማሰታውቂያ -
የዲስኘሊን ኮሚቴው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ያቀረበውን አቤቱታ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር ደርሶት መልስ እንዲሰጥበት በማዘዙ ክለቡ በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ለቀረበው አቤቱታ ባቀረበው መልስ የጨዋታው ሂደት ከDSTV ማስረጃው እንዲታይልን እኛ ያቀረብነው የዳኝነት መዛባት እንጂ በዳኛ ሊመደብ የሚችል መዋለ ንዋይ ሊታሰብ የማይችል መሆኑን በመግለጽ በአጠቃላይ የብሔራዊ ዳኞች ያቀረበውን የስም ማጥፋት ተግባር እንዳልሆነ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር አቤቱታ በግልፅ ባስቀመጠው ሃሳብ እንደሚያመላክተው የውድድሩ ዳኞች የተወሰኑ ክለቦችን ወደ ክብር ኮርቻ ለማስቀመጥ በሚመስል መልኩ ውድድሮች ላይ የሚመደቡ አንዳንድ ዳኞች መዋዕለ ንዋይ በመመደብ የአንድን ድርጅት ተወካይ ቡድን የድካምና የልፋት ውጤት የሚቀይር አነጋጋሪ የሆኑ ውሳኔዎች ይወሰናሉ በማለት ገልጿል፡፡
ክለቡ ይህን ለማለት የቻለበት ምክንያትና ማስረጃ እንዲሁም መልስ እንዲሰጥበት ተጠይቆ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ያቀረበው መልስ በጨዋታው ሂደት ዳኞች የፈፀሙት ጥፋት በDSTV ይታይልኝ፣ የዳኝነት መዛባት ማለቴ እንጂ በዳኛ ለመመደብ የሚችል መዋለ ንዋይ አይታሰብም በማለት ከነገሩ ለመሸሽ በማሰብ በሚመስል መልኩ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪ በዲስኘሊን መመሪያ አንቀጽ 80/22 መሰረት ክለቦች ለፌዴሬሽኑ የሚጽፋቸውን ደብዳቤዎች እውነተኝነትና ሕጋዊነት ማረጋገጥ ያለበት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ይሁን እንጂ ክለቡ ማስረጃ አቅርብ የተባለው አንዳንድ ዳኞች መዋለ ንዋይ በመመደብ ውጤት የሚቀይር ውሳኔ ይወስናሉ በማለት ያቀረበውን በተመለከተ ሆኖ እያለ የዳኝነት ውሳኔዎች አስመስሎ ማቅረቡ ፍፁም ተገቢነት የለውም፡፡ በተጨማሪም ክለቡ በገለፀው መሰረት ማስረጃ እስካላቀረበ ድረስ የፈፀመው የስም ማጥፋት ተግባር እንደሆነ ኮሚቴው ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
በሁለቱም የጨዋታ አመራሮች የቀረበው ሪፖርት ሲመረመር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ ስላቀረበው አቤቱታ የሚያስረዳ /የሚያረጋግጥ ምንም አይነት የቀረበ ሪፖርት የለም፡፡ አመልካች ክለቡም በወቅቱ ያቀረበው ቅሬታም ሆነ ክሰ የተመዘገበ አልተገኘም፡፡
በተጠቀሰው ቀን የተደረገውን ጨዋታ ቪዲዮ ሲታይ ክለቡ በጽሑፍ እንዳቀረበው የፌዴሬሽኑ ዳኞች ላይ እና በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ላይ ያቀረበው አስተያየት በእውነት ያልተመሰረተ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የዲስኘሊን ኮሚቴ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተሻሽሎ በወጣው የዲስኘሊን መመሪያ አንቀጽ 72 መሰረት የሚከተለውን ውሳኔ መስጠቱን ገልጿል።
ክለቡ ለፌዴሬሽኑ የሚጽፋቸውን ደብዳቤዎች በእውነተኝነትና ሕጋዊነት ማረጋገጥ ያለበትን ግዴታውን ባለመወጣቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር ብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) እንዲቀጣ እና እንዲከፍል ሲወስን ክለቡ ይህ ውሳኔ በደረሰው በ7 ቀናት ውስጥ እንዲፈጽም ታዟል፡፡