በሁለተኛው ዙር ጠብ በማያጣው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ትላንት በምድብ ሀ ረፋድ ላይ የነበረው ምንድነው ?

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የምድብ ሀ ጨዋታዎች በቢሾፍቱ ከተማ እየተደረገ ይገኛል። ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ቡድኖችን ለመለየት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በሚዘጋጀው በዚህ ውድድር ላይ ትላንት በኮንሶ ኒውዮርክ እና ኑዌር ዞንን አገናኝቶ የነበረው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ መጨረሻው ሳያምር አምስት ተጫዋቾች ወደ ሆስፒታል ያመሩበት ክስተት ተፈጥሯል።

በሁለተኛው ዙር ተመሳሳይ ድርጊቶችን እያስተናገደ እንዳለ የሚነገርለት ይህ ውድድር ትላንት ዕሁድ ጠዋት 3 ሰዓት ሲል ቢሾፍቱ ስታዲየም ላይ የሁለቱ ቡድን ጨዋታ መደረግ የቻለ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ኑዌር ዞኖች ጎል አስቆጥረው እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩ ሲሆን ከዕረፍት በኋላ ገና በአንደኛው ደቂቃ ኮንሶ ኒውዮርኮች ጎል አስቆጥረው ጨዋታው 1ለ1 በሆነ ውጤት በመጨረሻም ፍፃሜውን አግኝቷል።
ጨዋታው በሰላም ከተጠናቀቀ በኋላ በተጫዋቾች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ወደ መኪናቸው ሲያመሩ በነበሩ የኮንሶ ኒውዮርክ ተጫዋቾች እና የመኪናው ሾፌር እና ረዳት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ ደርሶ ወደ ሆስፒታል አምርተው ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን ባደረግነው የመረጃ ማሰባሰብ ስራ የኑዌር አሰልጣኝ እና የቡድኑ ተጫዋቾች የፈጠሩት አላስፈላጊ ድርጊት ለጠቡ መነሻ እንደሆነ ሰምተናል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በላቀ ደረጃ እግር ኳሷ አድጎ ነገ የተሻለ ማየትን ብንመኝም እንዲህ አይነት አስነዋሪ በድንጋይ እና ቦክስ የተነሳ የማይሆን ቦታ ላይ ሆኖ ማየታችን እጅጉን ያቆስላል።

በመጨረሻም ይህ ጥል የከፋ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ የቢሾፍቱ እግር ኳስ ወዳድ ህዝብ መመስገን እንዳለበት መረጃ ያደረሱን በጠቅላላ ነግረውናል።
አስተያየት ይስጡ