“ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፋችን ለእኛ ጥርጊያ መንገድ እንጂ ፍፃሜ አይደለም” አሰልጣኝ ስዩም ከበደ /ፋሲል ከነማ/

 

ፋሲል ከነማ በእስካሁኑ የፕሪሚየር ሊግ ጉዞው ስኬታማና የዋንጫ ቡድን መሆኑን እያሳየ ነው ከ15 ጨዋታ 12 ጊዜ አሸንፎ 2 ጊዜ አቻ ወጥቶ 1 ጊዜ ተረትቶ በ38 ነጥብና ግብ ሊጉን በርቀት እየመራ ይገኛል፡፡ ባለፉት 3 አመታት ቀጣይነት ያለውን አቋሙን ያሳየው ፋሲል ከነማ በ2013 የፕሪሚየር ሊጉ ባለ ድል እንደሚሆን በደጋፊዎቹ ታምኖበታል፡፡ ባህርዳር ላይ በነበረው ቆይታ 5 ጊዜ ተጫውቶ 4ቱን በድል አንዱን በአቻ ውጤት የፈፀመው የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ሊጉ ድል፣ ስለ ፋሲልና ሌሎች ተፎካካሪ ክለቦች፣ ስለ ዳኝነቱ፣ ስለ ዋንጫ ፉክክሩ፣ ስለ ሙጅብ ቃሲም፣ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና፣ ውጤቱ በቡድናቸው ላይ ስለፈጠረው አንድነትና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- አሁን የዋንጫውን እጀታ ይዣለሁ ለማለት ትደፍራለህ?

ስዩም፡- /ሳቅ/ አይ ገና ነው… 2ኛ ዙር የተጫወትነውኮ 3 ጨዋታ ብቻ ነው ገና 9 ጨዋታ ይቀረናል ቀጣይ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ላይ ሲካሄዱ ለሚኖረን አቋም የአየር ሁኔታ፣ ሜዳው፣ የልምምድ ሜዳው ሁሉ መታየት ያለባቸው ይመስለኛል፤ ቡድኔ ላይ የሚፈጥሩት አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ይመስላል? የሚለው የግድ መታየት አለበት፡፡ እንደ ቡድን ጥሩ ግስጋሴ አድርገናል ሻምፒዮናው ላይ ከሚፎካከሩት ዋነኞቹ ነን ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሀትሪክ፡- መታየት አለባቸው ካልከው ጉዳዮች ውጪ እንደ ቡድን ከባድ ነው የምትለው አለ?

ስዩም፡- ጥሩ የሚጫወት ቡድን ጥሩ የጨዋታ ሜዳና ጥሩ የልምምድ ሜዳ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲገኝ አቋሙን ጠብቆ መጫወት ደግሞ ከቡድኑ ይጠበቃል፤ ውድድር ብቻ ሳይሆን ልምምድ ላይ የሚኖረን አቋም ይወስነዋል፤ ድሬደዋ ላይ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል ሜዳው፣ የልምምድ ሜዳው እንዴት ነው በሚል አወዳዳሪው አካል በጥልቀት ሊመረምር ይገባል፡፡ በቀረፃውም በሁሉም ነገር እድገት እያሳየ ያለ የሊግ ውድድር ነውና ጥሩ ነገር ለማሳየት የተመቻቸ ነገር ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፤ ከዚያ ውጪ ግስጋሲያችንን ቀጥለናል 100% ዝግጁ ሆነን ለእያንዳንዱ ጨዋታ ትኩረት ሰጥተን እንገባለን እኛ ማድረግ የምንችለው ይህን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፏል፤ በሁለቱ ቡድኖች ደረጃ የሚፈትነን ቡድን አለ ብለህ ታምናለህ ?

ስዩም፡- አዎ… ሀዲያ ሆሳዕና፣ ወላይታ ድቻ፣ አዳማ ከተማ፣ ሲዳማ ቡናም ቀላል አይደሉም፤ ለዋንጫ ይሁን ላለመውረድ የሚጫወቱ ቡድኖች ይፈትናሉ፤ ሁሉም ቡድን ተጨዋች እያስፈረመ እየተጠናከረ ነው፤ ማንም የሚናቅ ቡድን የለም፡፡ ሻምፒዮን እንሆናለን ማለት ብቻ ሳይሆን ጠንክረን 100% ተዘጋጅተን መቅረብ አለብን ብዬ አምናለው፡፡ በርግጥም ኢትዮጵያ ቡና ሀዲያ ሆሳዕና ባህርዳር ከተማ ጠንካራ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በሙጂብ ቃሲም ውጤታማ አቋም ዙሪያ ምን ትላለህ?
ስዩም፡- ሙጅብ ቃሲም ባለፉት 4 አመታት የቡድኑ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ እየጨረሰ ነው ከ50 ግብ በላይ ማስቆጠርም ቀላል አይደለም ሙጅብ አሁንም የቡድናችን ትልቅ ሰው ነው በራሱ ደረጃ የሚጠበቅበትን እያደረገ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ሙጂብ ቃሲምን ስለያዘ እድለኛ ነው ማለት ይችላል?

ስዩም፡- ሙጂብ ብቻ አይደለም ሙጂብ ብቻውን ምንም ሊፈጥር አይችልም በዙሪያው ያሉትን ተጨዋቾች ተመልክት እነ ሽመክት፣ ሱራፌል፣ በዛብህ፣ ሳኛ፣ እንየው የኮቺንግ ስታፉን ጨምሮ ምርጥ ናቸው፤ እርሱም ጠንካራ ሆኖ ታቅፎ የሁሉም ድጋፍ ኖሮት የተገኘ የጋራ ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናን ስታሸንፍ ምን ተሰማህ?

ስዩም፡- ግጥሚያውን ከማሸነፍ ውጪ የተለየ ስሜት አልተሰማኝም… ፋሲል ከነማ ባለፉት አመታት ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ዘንድሮ በእኔ ዘመን ሻምፒዮን ሆኖ በክለቡ ታሪክ ትልቁን ዋንጫ ማንሣቱ ለኔ ክብር ነው፤ ከዚህ በላይ ድርብ ታሪክ የለም፡፡ ይሄ የሚሆው ጠንካራ ቡድኖችን ስናስቀር ነውና ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናንን ማሸነፋችን ለኛ ጥርጊያ መንገድ እንጂ ፍፃሜ አይደለም የበለጠ ጠንክረን እንድንገባ ግን አድርጎናል፡፡

ሀትሪክ፡- ለዋንጫ ከሚፋለሙትና ላለመውረድ ከሚጫወቱት ክለቦች የትኞቹ ይከብዳሉ?

ስዩም፡- ሁሉም አንድ ነው ባይ ነኝ፤ ላለመውረድ ስለሚተናነቅ 100% ትኩረት እንድትሰጥ ያደርግሃል በሻምፒዮናው የሚፋለሙን ክለቦችም ትኩረት ሰጥተን እንድንገባ ያደርገናል ለጊዮርጊስ 100% ተዘጋጅቼ ለአዳማ 40% እገባለሁ ማለት አይደለም፡፡ በፋሲል ከነማ የውድድር ቅርፅ ለሁሉም 100% ትኩረት ሰጥተን ነው የምንገባው፡፡

ሀትሪክ፡- ውጤታማ መሆናችሁ “ስዩም ይውጣ የሚሉትን ሁሉ ወደ አንድነት አምጥቷል ብለህ ታምናለህ?

ስዩም፡- መቶ በመቶ ሁሉንም ማለት በሚቻል አንድ አይነት አቋም እንዲይዝ አድርገናል ብዬ አስባለው፡፡ ውስን ደጋፊዎች ያልተመቻቸው ነገር ሊኖር ይችላል ወይም የራሣቸው ተልዕኮ ሊኖራቸው ይችላል ነገር ግን እየተመዘገበ ያለው ውጤታ ሁሉንም አሳምኖ ለአንድ ፋሲል በጋራ እንድንዘምር አድርጎናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ኮንትራትህ ዘንድሮ ይጠናቀቃል… ታራዝማለህ ወይስ?

ስዩም፡- ወቅቱ እርሱን ለመናገር አይፈቅድም ክለቤ የተሻለ የሆነውን ነገር እንደሚያሟላልኝ አውቃለሁ ግን አሁን ስለ ኮንትራቱ የማውሪያ ጊዜ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- ከዳኝነት ጋር ተያይዞ የምትለው ነገር አለ?

ስዩም፡- በተፈጥሮዬ ዳኝነት ላይ ቅሬታ ማቅረብ አልወድም ባህሪዬም አይደለም፤ ነገር ግን ዲ ኤስ ቲቪ ተጨዋቾችም አሰልጣኞችን እንደሚያስተምር ለዳኞችም ትምህርት ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፤ ያጫወቱትን ጨዋታ እየተመለከቱ ብዙ ሊማሩ ሊሻሻሉበት ይችላሉ፤ የዳኞች አስተማሪዎች ከዳኞቹ ጋር ሆነው ቢገመግሙና ቢማማሩ ለነርሱ ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እንደ አሰልጣኝ በክለቡ ተጫዋቾች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሬያለሁ ማለት ይችላል?

ስዩም፡- 100% ተፅዕኖ ፈጥሬያለሁ… አሁን ብቻ አይደለም 2012 ላይ ኮቪድ እስካቋረጠው ድረስ እየመራን ነው የተቋረጠው አሁንም ያንን እያስቀጠልን ነው ያለነው… ዘንድሮ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ስናደርግ ጥሩ ነገር ነው ያሳያነውና በዚህ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ልናገር አንዳንዴ አርዕስት የምታወጣው ለኔ አይመቸኝም፤ ይህን ካላሻሻልክ ዳግመኛ ኢንተርቪው ለመስጠት ይከብደኛል የኔን ፐርሰናሊቲ የሚያወርድ ከኔ የማይጠበቅ ነገር እዚያ ላይ መፃፍ የለበትም፤ ለምሣሌ የስዩም አንዱ እግር ተቆርጧል ብለህ ያልሆነ ነገር ብታወጣ ልክ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- አሪፍ ነገር ነው ያነሳኸው.. የስዩም እግር ሳይቆረጥ ተቆርጧል የሚል መረጃ አላወጣም ስዩም ከበደ ከተናገረው ውጪ ርዕስ መርጬ አላውቅም ከእኔ የሚጠበቀው ይሄ ነው…ቋሚ 11 ተጫዋች ምርጫ ላይ ማንም ጣልቃ ገብቶ እገሌን ምረጥ ማለት እንደማይችል ሁሉ አንተም የኔን ርዕስ የመምረጥ መብቱ አይኖርህም…እንደ ጋዜጠኛ የኔ መብት ነው፡፡

ስዩም፡- ለርዕስ ተጠንቀቅ የጮኸ ርዕስ ያየ አንባቢ ምን ነካው ብሎ ውስጡን ሳያነብ ሊሄድ ይችላል ይሄ ለእኔ ስም ጥሩ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- አሁን በሰራነው ቃለ ምልልስ ዙሪያ ርዕስ የምመርጠው እኔ ነኝ፤ ጣልቃ እንድትገባ አልሻም ነገር ግን ካልከው መሀል ርዕስ የማድረግ መብቴን እጠቀማለሁ፤ አንተ ካልከው ውጪ እንዳይሆን የማድረግ ግዴታዬን እወጣለሁ?

ስዩም፡- አመሰግናለሁ… እኔም የምፈልገው ይህን ነው መልካም ጊዜ የግል ሃሳቤን ነው የነገርኩህ
ሀትሪክ፡-አመሰግናለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport