በመሸሻ ወልዴ
ወልቂጤ ከተማ በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ውድድር ጅማሬው ከወዲሁ ጥሩ ጉዞን እያደረገ ይገኛል፤ ይሄን ውጤታማነታቸውን አስመልክቶም በአማካይ ስፍራው ላይ የሚጫወተው ፍሬው ሰለሞን /ጣቁሩ/ ከሀትሪክ ድረ- ገፅ ጋር ባደረገው ቆይታ ሀሳቡን ይናገራል፡፡
ወልቂጤ ከተማ ለዘንድሮው ቡድኑ ከያዛቸው የተጨዋቾች ስብስቡ መካከል አንዱ የሆነው ይኸው ተጨዋች በ4ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማን በቶማስ ስምረቱ ብቸኛ ግብ 1-0 ካሸነፉ በኋላም ስለቡድናቸው “አሁን የያዙትን ያለመሸነፍ ጉዞ በማስቀጠል ጠንካራ ቡድንን እንደሚገነቡ እና ውጤታማ የሆነን ቡድንም እንደሚሆኑ ለሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ከፍሬው ሰለሞን ጋር ሀትሪክ ድረ-ገፅ የነበራት አጠቃላይ ቆይታም ይህንን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ያለመሸነፍ ጉዞአችሁ ቀጥሏል፤ ስለ ቡድናችሁ እና እያስመዘገባችሁ ስላላችሁት ውጤት ምን ትላለህ?
ፍሬው፡- ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ጅማሬው ያለመሸነፍ ሪከርዱን በማስጠበቅ በአሁን ሰዓት ላይ ውጤታማ ሆኖ ያለው ኳሱን እንደ ቡድን ጥሩ ስለሚጫወት ነው፤ ከዛ በተጨማሪም ህብረቱና አንድነቱም ለውጤት እያበቃው ነው፤በቀጣይ ጨዋታዎች ይሄን ሪከርድም ለማስጠበቅ እንጫወታለን፤ ቡድናችንን በተመለከተ ስብስቡ በጣም ጥሩ ነው፤ ወጣትና ሲኒየር ተጨዋቾች ተቀላቅለው ይጫወቱበታል፤ ደስ የሚል ቡድንም ነው ያለን፡፡
ሀትሪክ፡- በሊጉ ከኢትዮጵያ ቡናና ከጅማ አባቡና ስትጫወቱ ብቻ ነው ነጥብን የጣላችሁት ውጤቱ አስቆጫችሁ?
ፍሬው፡- አዎ፤ ያገኘናቸውን የግብ እድሎች ካለመጠቀማችን አንፃር በጣም ተቆጭተናል፡፡
ሀትሪክ፡- ባህር ዳር ከተማን በ4ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ አሸነፋችሁ፤ በጨዋታው ላይ የነበረው ልዩነት ምን ነበር? ለድልስ እንዴት በቃችሁ?
ፍሬው፡- የጨዋታው ልዩነት ከእኛ በደረጃው ከፍ ብሎ የነበረውን ቡድን በእንቅስቃሴ ደረጃ በልጠን ማሸነፋችን እና ያለመሸነፍ ሪከርዱንም ማስቀጠል መቻላችንም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ባህር ዳርን ገጥማችሁ አሸነፋችሁት፤ ስለ እነሱ ምን ትላለህ?
ፍሬው፡- ባህር ዳር ከተማ ጠንካራ የሊጉ ቡድን ነው፤ ከእኛ ጋር ሲጫወቱ ግን በፊት፣ በመሀል እና በመስመር እንቅስቃሴው በኩል ያላቸውን ጥሩ ጎን ልንዘጋባቸውና ልንገድብባቸው ስለቻልን እንደዚሁም የኳስ ብልጫውንም ስለወሰድንባቸውም ግጥሚያውን ለማሸነፍ ችለናል፡፡

ሀትሪክ፡- የክለባችሁ ጠንካራ እና ደካማ ጎናችሁ ምንድን ነው?
ፍሬው፡- ህብረታችንና አንድነታችን ነው ጠንካራው ጎናችን፤ ደካማ ጎናችን ደግሞ ስንጫወት ችኮላና ጥድፍያን የምናሳይ መሆናችን ነው፤ ይሄም ችግር እንዲቀረፍ ታዳጊ የሆኑ ተጨዋቾቻችንን ልምድ ካላቸው ተጨዋቾች ጋር በማቀናጀት እና የክለቡንም ድክመት በማወቅ ጠንካራ ቡድንን ለመገንባት እየተዘጋጀን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤ በሊጉ የት ድረስ ይጓዛል?
ፍሬው፡- ዓላማችን ሊጉን ከ1-3ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ መቻል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በሊጉ ለእናንተ ፈታኝ የሚሆንባችሁ ቡድን ማን ነው?
ፍሬው፡- እስካሁን በደረጃው ሰንጠረዥ ከላይ ያሉትን ቅ/ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማንና ሀድያ ሆሳህናን ያላገኘናቸው ቢሆንም የእኛ ክለብ እነሱን ሲያገኝ ኳሱን እንደ ህብረት ጥሩ አድርጎ ስለሚጫወት ፈታኝ ይሆንበታል ብዬ የምገምተው ክለብ የለም፡፡
ሀትሪክ፡- በዝውውር መስኮቱ ወደ ወልቂጤ ከተማ አምርተህ ነው እየተጫወትክ የምትገኘው፤ ቡድኑ ትክክለኛው ምርጫህ ነው?
ፍሬው፡- አዎን፤ ለዛም ነው ምንም እንኳን ከሐዋሳ ከተማና ከሲዳማ ቡና እንደዚሁም ደግሞ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በብዛት ብነጋገርም በተለያዩ የራሴ ምክንያቶች ነው ምርጫዬንና ውሳኔዬን ለወልቂጤ ከተማ በማድረግ እና ከእነሱም ጋር የዝግጅት ወቅቱን በተሻለ መልኩ ስለሰራውም ቡድኑን የተቀላቀልኩት፡፡
ሀትሪክ፡- ከሲዳማ ቡና ጋር በቀጣይነት የምታደርጉትን ጨዋታ እንዴት እየጠበቃችሁት ነው?
ፍሬው፡- አሁን የምናደርገው ጨዋታ ካለፉት ግጥሚያዎቻችን የተለየ አይደለም፤ እኛ ለሁሉም ቡድንም ነው እኩል ትኩረት ሰጥተን ነው የምንጫወተውና ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፤ ከፊት ከፊት ያሉትን ጨዋታዎች ስናሸንፍም ነው ስለ ዋንጫና ከ1-3 ባሉት ደረጃ ውስጥም ሊጉን ስለመጨረስም ነው የምናስበው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?
ፍሬው፡- ወልቂጤ ከተማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ውጤት እያመጣ ያለው እንደ ግል ሳይሆን እንደ ህብረት በጋራ በመጫወቱ ነው፤ ይህ አካሄዱ ተጠናክሮም ሊቀጥል ይገባል፤ ከዛ ውጪ ማለት የምፈልገው ለእዚህ ቡድን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ አቅሜ በሚችለው መልኩ ምርጥ ግልጋሎቴን ለመስጠት መዘጋጀቴን ነው፡፡
አስተያየት ይስጡ