“በቶፕ አራት ውስጥ ሊጉን ለመጨረስ ጊዜው አልረፈደብንም”ደስታ ዩሃንስ /ሐዋሳ ከተማ/

“በቶፕ አራት ውስጥ ሊጉን ለመጨረስ ጊዜው አልረፈደብንም”

“የሐዋሳ ከተማ ስምና ዝና በእኛ የተጨዋቾች ዘመን መመለሱ አይቀርም”።ደስታ ዩሃንስ /ሐዋሳ ከተማ/

ሐዋሳ ከነማ ወላይታ ድቻን 3-2 ካሸነፈ በኋላ የቡድኑ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ደስታ ዩሃንስ ስለ ጨዋታው፣ ስለ ቡድናቸው፣ እያስመዘገቡት ስላለው ውጤት፣ ስለራሱና ሌላ ተያያዥ ጥያቄን የሀትሪክ ስፖርቱ ድረ-ገፅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አቅርቦለት ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቷል።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የክለባቸውን የዘንድሮ የውድድር ዘመንን ተሳትፎ በተመለከተ

“በአብዛኛው ጨዋታዎቻችን ቡድናችን በወጣት ከመገንባቱ አኳያ በጣም ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴን እያደረግን ነው። ኳስን ገና ካቆመ ከሁለት ዓመት በፊት በሆነው አሰልጣኛችን ሙሉጌታ ምህረት አማካኝነትም እየሰለጠንን እንደ አጠቃላይ ያውም ከጥቅማ ጥቅምና ከደመወዝ ክፍያችን አኳያ ነገ ዛሬ ይሰጣችኋል እየተባልንና ብዙ ችግሮች ኖሮብን ለክፉ የማይሰጥ ውጤትን እያስመዘገብን መሆኑ እየረዳን ያለውን ፈጣሪን እንድናመሰግነውም ነው እያደረገን ያለውና አሁንም ከዚህ በላይ ከፍ እንድንል የክለባችን የበላዮች በብዙ ነገሮች ቢያግዙን ጥሩ ነው”።

የውድድር ዘመኑን ሲጀምሩ አቅደው ስለነበረው ነገር

“እልማችንና ግባችን በቶፕ አራት ውስጥ ሆነን ውድድሩን ለመጨረስ ነበር። አሁን ላይ ግን ከዛ ባነሰ ደረጃ ላይ ብንገኝም ያን ደረጃ ይዘን ለመፈፀም ጊዜው አልረፈደብንምና ቀሪዎቹን ጨዋታዎቻችንን በማሸነፍ ይህን እልም ለማሳካት ጥረትን እናደርጋለን”።

ወላይታ ድቻን ስላሸነፉበት ጨዋታ

“እንዲህ ያለ ጨዋታን ከውጪ ሆነህ ስትመለከተው ቀለል ያለ ሊመስልህ ይችላል። ዲቻዎች ግን ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አጥቂዎቻቸውን ሳያሰልፉ ቀርተው ሁለቱን ተጠባባቂ በረኞቻቸውን ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ አጥቂ አድርገው በማጫወት ስለተጠቀሙባቸው እኛን በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ጫናን እንድናስተናግድና በእንቅስቃሴ ደረጃም እንድንወርድ ስላደረግን ጥሩ እንዳንጫወት አድርጎን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ክፍተቶቻችንን አርመን በመግባት ጨዋታውን ልናሸንፍ ችለናል”።

ድሉ ይገባቸው እንደሆነና እሷንም የአሸናፊነት ግብ ስለማስቆጠሩ

“አዎን በጨዋታው እኛ በንፅፅር ከእነሱ እንሻል ስለነበር ድሉ ይገባናል። እኔም የድሏን ግብ ስላስቆጠርኩ በጣም ደስ ብሎኛል”።

ስለ ሐዋሳ ከተማ ክለብ ቆይታው

“ይሄ ቡድን ለ6 ዓመታት ያህል የቆየሁበትና አሁንም እየተጫወትኩበት ያለ አሳዳጊዬ እንደዚሁም ደግሞ ማንነቴና ከማንም በላይ የምወደውም ቡድኔ ነው፤ ለእኔ ክለቡ ሁሉ ነገሬ ስለሆነም ስለ ቡድኑ ብዙ ለማለት ቃላቶችም ነው የሚያጥረኝ። ከአንድ ዓመት በፊት ብቻም ነው ወደ መከላከያ በማምራት ልጫወት ከቻልኩ በኋላ ክለቡ ወደ ሱፐር ሊግ ሲወርድ እኔም ተመልሼ ወደ ቀድሞ እናት ቡድኔ ላመራ የቻልኩት”።

ስለ ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ

“በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ የእዚህ ቡድን ማለፍም ለሁላችንም የሀገራችንን ተጨዋቾችና በቀጣይነት ለሚመጡ ታዳጊ ተጨዋቾችም ከፍተኛ መነሳሳትን የሚፈጥርም ነው። የአሁኑ ድል ከዚህ ቀደም ከ31 ዓመታት በኋላ እንዳለፍነው ያን ድል የሚያስታውሰን ነው። ከዛ ውጪም የቡድኑ ማለፍ በራሱ እኔንም በጉዳት ምክንያት ከራቅኩበት የዋልያዎቹ የቀድሞ ስብስብ ዳግም እንድመለስ እያስመኘኝምና ለዛም ጠንክሬ እሰራለሁ”።

ስለ ትዳር ህይወቱ

“በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ የትዳር ህይወቴን እየመራው ነው። ባለቤቴም ቤዛዊት ሰለሞን ትባላለች። እሷ ካለፉት 10 ዓመታት አንስቶም አብራኝ በፍቅር የቆየች እና ከአንድ ዓመት በፊት ደግሞ ጋብቻን ፈፅመን የዘጠኝ ወር ልጅን ያፈራን ስለሆነ ያ ለእኔ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሮልኛል። ባለቤቴን በተመለከተ እሷ ከፈጣሪ በታች ለእኔ የእግር ኳስ ህይወት ብዙ ነገሮችን እያደረገችልኝ የመጣች ናት። በጣምም ነው የምወዳት። ለእሷ ከፍተኛ ምስጋናም ይገባታል”።

በመጨረሻ

“ሐዋሳ ከተማን በውጤት ደረጃ አይቀርም ወደፊት የተሻለ ደረጃ ላይ እናደርሰዋለን። የቀድሞ ስሙና ዝናውም በእኛ የተጨዋችነት ዘመን ወደነበረበት ይመለሳል”

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website