“አልሸነፍ ባይነታችንን ስላስቀጠልንና መሪም ስለሆንን ሁሉም ቡድኖች ለእኛ ስለውና ተዘጋጅተው ነው እየመጡ ያሉት”ዳዋ ሁጤሳ /ሀዲያ ሆሳዕና/

ሀዲያ ሆሳዕና በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና አራት ጨዋታዎችን በማሸነፍ እና አንድ ጨዋታን ደግሞ አቻ በመለያየት በሊጉ የመሪነት ስፍራ ላይ ተቀምጧል፤ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ይኸው ቡድን እስካሁን ባደረጋቸው አምስቱ ተከታታይ ጨዋታዎች ባለመሸነፍ ሪከርድም የተጓዘ ብቸኛው ቡድን ሲሆን በአምስተኛው ሳምንት የሊጉ መርኸ ግብርም ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያደረገውን ጨዋታም ብቻ ነው ነጥብ በመጣል በጥንካሬው እየተጓዘ የሚገኘው፡፡

የሀዲያ ሆሳዕናን የውጤታማነት ሚስጥር በተመለከተ፣ ቡድኑ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ስለመምራቱና ስለ ቀጣይ የውድድር ተሳትፎአቸው እንደዚሁም ደግሞ ከራሱ ጋር በተያያዙ ጥያቄዎች ዙሪያ ለቡድኑ ጎል እያስቆጠሩ ካሉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን ዳዋ ሁጤሳን የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ላቀረበለት ጥያቄዎች ሁሉ ተጨዋቹ ምላሹን ሰጥቷል፤ በሚከተለው መልኩም ቀርቧል፡፡

የሀዲያ ሆሳዕና የእስካሁኑ የውጤታማነት ሚስጥር እና ሲዳማ ቡናን ስላሸነፉበት ጨዋታ?

“የቤት ኪንግ የፕሪምየር ሊጉ የውጤታማነት ጉዞዋችን በጣም አሪፍ እና ለብዙዎችም መነጋገሪያን የፈጠርንበት ነው፤ በእስካሁኑ ጨዋታችንም አራት ጨዋታዎችን አሸንፈን በአንዱ አቻ ተለያይተናል፡፡ ያለ መሸነፍ ሪከርዳችንን በማስጠበቅም እኛ ብቸኛው ቡድን ሆነናል፤ ከዚያም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በእዚህ መልኩ በተሳካ የውጤት ደረጃ በመጓዝም የሚከብደውን ነገርም እያስመዘገብንም ይገኛል፡፡ የእዚህ የውጤታማነት ሚስጥራችንም ቡድናችን ጠንካራ ቡድንን ስለገነባ እና አጥቅቶም የሚጫወት ቡድን ስለሆነ ነው፡፡ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ስለዳረግነው ጨዋታ ደግሞ ቡድናችን በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበረም፤ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ተሽለን መጥተን ግብ ብናስቆጥርም የትኩረት ማነስ /ኮንሰንትሬሽን/ አጥተን ግጥሚያውን በአቻ ውጤት አጠናቀቅናል፤ ይሄን ነጥብ እንድንጥል ያደረገንም በአሁን ሰዓት በርካታ ቡድኖች እኛ የሊጉ መሪ መሆናችንን ስለሚያውቁና ባለመሸነፍ ሪከርዱም እየተጓዝን ስለሆነ እኛ ላይ ከፍተኛ ትኩረትን አድርገው የሚመጡበት ሁኔታም ስላለ ነው”፡፡

ስለ ተጋጣሚያችሁ ወልቂጤ ከተማ

“ወልቂጤ ከተማ ጥሩ ቡድን ነው፤ የሚያምር የኳስ ፍሰትንም በመጫወት ላይ ይገኛሉ፤ ከዛም በተጨማሪ እስከአሁን ከገጠምናቸው ቡድኖችም ተጭኖ በመጫወት እነሱ የተሻሉ ናቸው፡፡ እነሱ ላይ ያየሁት አላስፈላጊ ነገር ከእኛ ጋር ሲጫወቱ ለውሳኔ ተገዥ ባለመሆን ዳኛን የመክበብና የመጫን ነገርን ነው፤ ወልቂጤን ብቻ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ በሊጉ የሚገኙትን ብዙ ቡድኖችን አሁን ላይ ስመለከት እኛ እያሸነፍን ከመምጣታችን አኳያ በአሁን ሰዓት በጣም ጠንካራ እየሆኑብን ነው የመጡት፤ ወራጅ ላይ ያለው ቡድን በራሱ ከባድ ነው የሚሆንብንና ከእዚህ በኋላ በሚኖሩን ጨዋታዎች እኛም በጣም ጠንክረን መምጣት እንዳለብንም ነው ለመረዳት የቻልነው”፡፡

በቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ የእዚህ ዓመት እቅዳችሁ ምንድነው? አሁን እያስመዘገባችሁት ካለው ውጤት አኳያስ ተገማች ቡድን ነበራችሁ?

“የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ሲጀመር የትኛውም ቡድን እንደሚይዘው ዓመታዊ እቅድ ሁሉ እኛም የት ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚኖርብን እናውቃለን፤ የአሁኑን ግን ገና ከጅማሬያችን ስናየው ካሰብነው በላይ ለመጓዝ እንደምንችል እየተደራን ስለሆነና እስከ ሻምፒዮናነትም ደረጃ ሊያስጉዘን የሚችልን ነገር ስለተመለከትን ይሄን የውጤታማነታችንን ሚስጥር አስቀጥለን እንሄድበታለን”፡፡

የሀዲያ ሆሳዕና ጥንካሬው እና ክፍተቱ

“የእኛ ትልቁ ጥንካሬ ጎል ጋር እንደርሳለን፤ ያገኘነውንም ጎል እናስቆጥራለን፤ ጉድለታችን ወይንም ደግሞ ክፍተታችን ብዙ ባይኖርም ኳስ ፍሰቱ ላይ ግን በደንብ ሰርተን በመምጣት የበለጠ ጥንካሬያችንን እናሳምራለን”፡፡

ሀዲያ ሆሳዕና በእዚህ አመት ከአንተ ምን ይጠበቅ?

“ጎል ነዋ! ያውም በየጨዋታው፤ ያ አልፎ አልፎ ካልተሳካ ደግሞ ለጓደኞቼ የግብ ኳሶችን በማቀበል /አሲስት በማድረግ/ መርዳትና ቡድኔን ደግሞ በሁሉም መልኩ ጥሩ በማገልገል ክለባችን እስከ ሻምፒዮንነት ደረጃ እንዲጋዝ የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለው”፡፡
በቤት ኪንግ የዘንድሮ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችሁ…. ላይ የድል ግብን በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ ካስቆጠርክ በኋላ ወደ ደጋፊዎቻችሁ ሄደህና እነሱን አቅፈህ ደስታህን በመግለፅህ

ከኮቪድ ፕሮቶኮል አኳያ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተህ ነበር….

“በእግር ኳስ አንድ አንዴ እንዲህ ያሉ የድል ግቦችን በምታገባበት ሰዓት ስሜታዊ ያደርግሃል፤ እኔም በጨዋታው ስሜታዊ ሆኜ ያንን በማድረጌ የዕለቱ ዳኛ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥቶኛል፤ ዳኛውም ትክክል ስለነበር ነው ከሜዳ ያስወጣኝ፤ እኔ ነኝ ለየክለቡ በክለብ ደረጃ የተሰጠውን የኮቪድ መመሪያን ስላላከበርኩ ከሜዳ የወጣሁትና አጥፍቻለው”፡፡

ከእዚህ በኋላ ከአዲስ አበባ ስታድየም ውጪ ስለመጫወታቸው?

“የሊጉን ቀጣይ ጨዋታዎች ወደ ጅማ እና ባህር ዳር ስታድየም ሄደን መጫወታችን ለእኛ ጥሩ ነው፤ ሜዳዎቹም ከአዲስ አበባ አንፃር በጣም ጥሩም ናቸው፤ ኳስን በደንብ አንሸራሽሮም ለመጫወት እንድንችል ያደርገናልና ይሄ ለቡድናችን ጥሩ አጋጣሚም ነው ሊሆንልን የሚችለው”፡፡

ሀዲያ ሆሳዕናን በቤት ኪንጉ ፕሪሚየር ሊግ ማንና የትኛው ቡድን ይፈትነዋል?

“ሁሉም ቡድኖች ጠንካራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ክለቦችም ከእዚህ በፊት ለቅ/ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ቡና የሚሰጡትን ግምትም ነው አሁን ላይ ለእኛ የሚሰጡትና በየጨዋታው ከእዚህ በኋላ ሁሉም ክለቦች ናቸው ለእኛ ፈታኝ የሚሆኑብን”፡፡
እንደ አጥቂ ኮከብ ግብ አግቢነትን ብዙዎች ይመኙታል፤ ዳዋስ ?
“እኔም እመኛለው፤ ዘንድሮ ትልቁ እቅዴም እሱን ማሳካት ነው፡፡ ብዙ ጎሎችን አስቆጥሬም ባለ ክብሩ መሆንን እፈልጋለሁ”፡፡
የሀዲያ ሆሳዕና የተጨዋቾች ስብስብን አስመልክቶ
“በየቦታው ጥሩ እና የተሻሉ ተጨዋቾች አሉን፤ ከእዚህ ስብስብ ጋር ሆነንም ብዙ የምንጓዝም ይመስለኛል”፡፡

በመጨረሻ

“ሀዲያ ሆሳዕና ጥሩ ቡድን ነው፤ ከእዚህ በኋላም ውጤታችንን በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ማስጠበቅ ይኖርብናል፤ በወራጅ ቀጠና ላይ ለሚገኙትም ሆነ ለሌሎቹ ቡድኖች እኩል ግምትን ልንሰጥ ስንችልም ነው የሻምፒዮናነቱን ዋንጫ ልናነሳ የምንችለውና ለእዚህ በጥንካሬችን እንጓዛለን”፡፡

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor