“ከዋንጫው ይልቅ ለወራጅነት ያለው ፉክክር ያጓጓል”በረከት ደስታ /ፋሲል ከነማ/

 

“ከዋንጫው ይልቅ ለወራጅነት ያለው ፉክክር ያጓጓል”

“ጎል ካስቆጠርኩ በኋላ ኳሷን ሆዴ ውስጥ የከተትኩት ባለቤቴ የዘጠኝ ወር እርጉዝ በመሆኗ ነው”

በረከት ደስታ /ፋሲል ከነማ/

በኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ፋሲል ከነማ ሐዋሳ ከተማን በበረከት ደስታና በአምሳሉ ጥላሁን /ሳኛ/ ሁለት ግቦች በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዮቹ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስም ያለውን የነጥብ ልዩነትንም ወደ 7 አስፍቶታል።
ፋሲል ከነማ ሐዋሳን ድል ካደረገበት ጨዋታ በኋላ የሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ በጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ አማካኝነት ለክለቡ ጎል ያስቆጠረውን በረከት ደስታን አናግሮታል። ተጨዋቹም ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል።

ድል ስላደረጉበት ጨዋታ

“በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፤ ከፍተኛ ተነሳሽነትም ስለነበረን ጎልም አስቆጥረናል። የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ደግሞ በሜዳው ላይ ከነበረው ሙቀት ጭምር ልንዳከም በመቻላችን ሐዋሳዎች በተራቸው ጥሩ ሊጫወቱ ችለዋል። ያም ሆነ ይሄ ግን እኛ ውጤቱን በጣም እንፈልገው ስለነበር ግጥሚያውን በማሸነፋችን ደስ ብሎናል”።

የድል ውጤቱ ይገባቸው እንደሆነ

“አዎን ይገባናል። ምክንያቱም ብዙ የግብ ዕድሎችን የፈጠርነው እኛ ነበርንና እነሱ ግን ሁለት ኳስ ነው የሞከሩት አንዱንም ተጠቀሙበት”።

ስለ ተጋጣሚያቸውን ሐዋሳ ከተማ

“ተሸንፈው ስለመጡ እነሱን እንደ ሌሎች ተጋጣሚ ቡድኖች አላከበድናቸውም። ለዛም ነው ያሸነፍናቸው። ከእረፍት በኋላ ግን ጥሩ በመጫወት የኳስ ብልጫን ወስደውብናል”።

ፋሲል ከነማ የሊግ ዋንጫውን ከፍ አድርጎ ያነሳ እንደሆነ

“መቶ ፐርሰንት ስልህ! ዋንጫውን እኛ ነን የምናነሳው”

ግብ አስቆጠርክ እና ኳሷን ሆድህ ውስጥ ከተትክ

“የእውነት ነው ባለፈው ድሬዳዋ ከተማ ላይ ሳስቆጥር ነበር ይህን ለማድረግ ፈልጌ የነበረው። ያም ሆነ ግን ረሳሁት። በእሁዱ ጨዋታ ላይ ግን ሐዋሳን ስናሸንፍ ባለቤቴ ቤዛዊት ሽመልስ የዘጠኝ ወር እርጉዝ ስለነበረች እና ልትወልድም ስለተቃረበች ያን አስቤ ነው ግብ ካስቆጠርኩ በኋላ ኳሷን
ሆዴ ውስጥ ልከታት የቻልኩት”።

ልጅህ ሲወለድ ወይ ስትወለድ ምን አስብሃል?

“ፈጣሪ ካለ እንደ እሁዱ ነው በድጋሚ ሶስተኛ ግቤን አስቆጥሬ ለልጄ ማስታወሻን ነው ማድረግ የምፈልገው”።

ኢትዮጵያ ቡናን እና ቅ/ጊዮርጊስን በ7 ነጥብ ልዩነት ስለመምራታቸው

“አዎን። በዚህ ደረጃ እንድንርቃቸው የእሁዱ ድል በጣም ያስፈልገን ነበር። ምክንያቱም ከአንድ ጨዋታ በኋላ ሁለቱንም ለጨዋታ በጣም በሚያመቸው የባህርዳር ስታድየም ሜዳ ላይ ስለምናገኛቸው እና ስለምናሸንፋቸው ያኔም የነጥብ ልዩነቱን የበለጠ አርቀነው ሻምፒዮናነቱን በጊዜ ለማወጅ እየተዘጋጀን ነው የምንገኘው”።

ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በአንተ እይታ

“የፕሪምየር ሊጉን ውድድር ስመለከተው ከዋንጫው ይልቅ ብዙ ቡድኖች በተቀራረበ የነጥብ ልዩነት ላይ ስለሚገኙ እና እርስ በርስም ስለሚጫወቱ ለወራጅነት የሚደረገው ፉክክር ያጓጓል፤ እነሱ ከዚህ በኋላ የሊጉ ድምቀትም ናቸው”።

ስለ ራሱ ወቅታዊ አቋም

“ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻልኩ መጥቻለሁ። የድል ጎሎችንም ለቡድኔ እያስቆጠርኩ ነው። በቀጣይነት ሌሎች ጎሎችንም አገባለሁ”።

 

ስለ ክለባቸው አዝናኙ ተጨዋች

“እሱ ባይኖር ምን ይውጠን ነበር። ጓደኛዬ ሽመክት ጉግሳ ነው ለሁላችንም ለዛ ያለው ጨዋታን እያመጣልን ደስታን የሚፈጥርልን”።

ስለ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ

“በጣም የተመቸኝ አሰልጣኝ ነው። የሚሰጠን ስልጠናና የሚከተለው አጨዋወትም ደስ ይላል። በተለይ ደግሞ ለእኔ ጥሩ ሳልሆንም ሆንኩኝም ብዙ ጠብቆኝ ጭምር የመጫወትን እድሎችን ሊሰጠኝና ስላለኝ አቅምም ነግሮኛል እና በዚህ ላመሰግነው እፈልጋለሁ”።

በመጨረሻ…

“ፋሲል ከነማ ከተከታዮቹ ቡድኖች ከወዲሁ ነጥቡን እያሰፋ እየሄደ ባለበት ግስጋሴው በጣም ደስ ብሎኛል። ይሄ ድሉም ይቀጥላል። ውጤቱ የመጣሁም በሁሉም ተጨዋቾች ጥረት እና በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እና የኮቺንግ ስታፉ የጋራ ጥረት ስለሆነም ለዚህ ውጤት ላበቃን ፈጣሪ ጭምር ታላቅ ምስጋናን ነው የማቀርበው”።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *