ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍንበት የዛሬው ድል በፖለቲካና በብዙ ነገር የታመሰችሁን ውዲቷን ሀገራችንን አንድ ያደረግንበት ቀን ናት” የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ አስቻለው ታመነ

“ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍንበት የዛሬው ድል በፖለቲካና በብዙ ነገር የታመሰችሁን ውዲቷን ሀገራችንን አንድ ያደረግንበት ቀን ናት”
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ አስቻለው ታመነ

ዋልያዎቹ ከኮትዲቯር አቻቸው በአቢጃን ያደረጉትን ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ 3-1 እየተመሩ ግጥሚያው የዕለቱ ጋናዊው አልቢትር ታሞ ሜዳ ላይ በመውደቁ ቢቋረጥም ማዳጋስካር ከኒጀር ጋር የነበራትን ጨዋታ ያለ ግብ በማጠናቀቋ ዋልያዎቹ ቀደም ሲል ያጠራቀሙት 9 ነጥብ ጠቅሟቸው በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ቀደም ሲል ማለፏን ካረጋገጠችው ኮትዲቯር ጋር ሊያልፉ ችለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ተከትሎ መላው ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለፁ ሲሆን እኛም ከጨዋታው በኋላ የብሄራዊ ቡድናችንን ተከላካይ አስቻለው ታመነን አጠር ያለ ጥያቄን አቅርበንለት ምላሹን ሰጥቶናል።

ለአፍሪካ ዋንጫ አለፍን እንኳን ደስ አለን?

“አመሰግናለሁ፤ እንኳን አብሮ ደስ አለን”።

ዋልያዎቹን በአፍሪካ ዋንጫ ከዚህ በፊት ተመልካች ሆነህ ሲያልፉ አይተሃል፤ አሁን ደግሞ በተጨዋችነት ዘመንህ ራስህ ለቡድኑ እየተጫወትክ ሲያልፉ ተመልክተሃልና ስሜቱ እንዴት ነው?

“በሁለቱም ሁኔታዎች ሀገሬ ለአፍሪካ ዋንጫው ያኔም ሆነ አሁን በማለፏ በጣም ብደሰትም የቡድኑ ተጨዋች እና አባል ሆኜ በዚህ ዘመን ላይ ደግሞ ደስታውን ስመለከተው የማላውቀው አይነት ስሜት ነው ሊሰማኝ የቻለው። ምክንያቱም ለዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ መቻላችን ለአገራችን ብዙ ትርጉም ነው ያለው። አገራችን አሁን ላይ ያለችበት ሁኔታ በጣም ያሳዝናል። በፖለቲካ እና በብዙ ነገሮች የታመሰችውን ይህቺውን ውዲቷ ሀገራችንን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን አንድ ያደርገናል ብዬ ስለማስብ ነው የደስታዬ መጠን ከፍ ሊል የቻለው”።

በመልበሻ ክፍል የነበራችሁ ደስታ ይገርም ነበር፤ የአንተም ለየት ይል ነበር?

“የእውነት ነው ደስታዬን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ ነበር ስጨፍር የነበርኩት፤ ግን ሁሉም ነበር በአስገራሚ መልኩ ሲደሰት የነበረው። ዛሬ ያልጠበቅኳቸው ተጨዋቾች ሁሉም ነበር ሲደሰቱም የነበረው እና ፈጣሪ የልፋታችንን አውቆም ነው ለታላቁ የውድድር መድረክም ሊያበቃን የቻለው፤ ለዛ ስላበቃንም ለእሱ ታላቅ ምስጋና ይግባው”።


ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እልማችሁ እንደሚሳካ አስቀድማችሁ ተናግራችሁ ነበር፤ ይሄ እንዴት እውን ሊሆን ቻለ?

“የዋልያዎቹ የአሁኑ ስብስብ በጣም አቅም እንዳለው እና ጥሩ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ተጨዋቾች በስኳዱ ውስጥ እንደያዘና ቡድኑም የሚከተለው አጨዋወት ጥሩ እንደነበርም ያስታውቅ ነበርና ለዛም ጭምር ነው የአሰልጣኙንም የጨዋታ ታክቲክ በመተግበሩም ላይ መጥፎ ስላልነበርን በአጠቃላይ ባላጠናቀቅነው እና ጥቂት ደቂቃዎች በቀሩበት ጨዋታ ላይ የማዳጋስካር ከኒጀር ጋር አቻ መውጣቷን ተከትለን ባለን የ9 ነጥብ ውጤት ብቻ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ልናልፍ የቻልነው”።

በመጨረሻ

“ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ማለትን እፈልጋለሁ”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website