“ጠንካራ ነን፤ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥም የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና የመሆን እቅድ አለን” ሰኢድ ሀሰን/ፋሲል ከነማ/

“ጠንካራ ነን፤ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥም የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና የመሆን እቅድ አለን”

“ጉዳት ሲደርስብኝ ከኳስ የምለይ መስሎኝ ሰግቼ ነበር”ሰኢድ ሀሰን/ፋሲል ከነማ/

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉሻምፒዮና ፋሲል ከነማ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ አንስቷል፤ ፋሲል ከነማ ይህን ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎም በቡድኑ ተጨዋቾችና በደጋፊዎቹ ዘንድ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ሊፈጠርም ችሏል፤ በክለቡ የአጭር ጊዜ የውድድር ተሳትፎ ታሪክ ከዚህ ቀደም የጥሎ ማለፍና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ለማንሳት የቻለውና አሁን ላይ ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ፋሲል ከነማ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ለመሆንም ክለቡ እቅድን የነደፈ ሲሆን ይህን እልም ለማሳካትም ከወዲሁ ጠንካራ ስራ እንደሚጀምሩ የቡድኑ ተጨዋች ሰይድ ሁሴን ከሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ባደረገው ቆይታ አስተያየቱን ሰጥቷል፤ ሁለቱ በቃለ-ምልልስ ያደረጉት ቆይታም ይህን ይመስላል፤ ተከታተሉት፡፡

ስለ ሻምፒዮናነታቸው

“በጣም ከምነግርህ በላይ ነው ደስተኛ የሆንኩት፤ ፋሲል ከነማ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ይህ ውጤት ይገባውም ነበር፤ የመጀመሪያውን ዓመት ሂ-ሰባዊና እግር ኳሳዊ ባልሆነ መንገድ ነው በደል ደርሶብንና ፍትህም ተነፍገን ዋንጫውን ልናጣው የቻልነው፤ የዓምናውን ደግሞ ሊጉን እየመራን በኮቪድ 19 ምክንያት ጨዋታዎቹ ስለተቋረጡ ሻምፒዮና ልንሆን የምንችልበትን ውጤት አጣን እንጂ ከነበረን ብቃት አኳያ በትክክል ድሎቹ ለእኛ የሚገቡን ነበሩ፤ ያም ሆኖ ግን በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፍ በጀመረበት ዓመት ላይ ይህንን የእስከዛሬ የልፋታችንን ዋንጫ ፍትሃዊ በሆነና ሁሉንም ባሳመነ መልኩ እንደዚሁም ደግሞ ስለበደላችንም ሁሉም ባወቀበትና ስለ ሀዘናችንም በተረዳበት ሁኔታ የሻምፒዮናነቱን ድል ልናገኝ በመቻላችን ደስታዬን የተለየ አድርጎታል”፡፡

ቤትኪንጉን በሻምፒዮናነት እንዲያጠናቅቁ ስለረዳቸው ነገር

“ለእዚህ ውጤት እንድንበቃ ያደረገንን ፈጣሪዬን ዓላ ነው በቅድሚያ ስሙን ጠርቼ የማመሰግነው፤ ለሁሉም ተጨዋቾቻችንም ሆነ አሰልጣኞቻችን እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎቻችንን ጨምሮም እንደየ እምነታችን አምላኮቻችን ለውጤታችን ማማር ረድተውናል፤ ከዛ ቀጥዬ ለድሉ እንድንበቃ ያደረገን ባለፉት ሁለት ዓመታት ይህን ውጤት ማግኘት እየቻልን ከላይ በገለፅኳቸው መልኩ ውጤቶቹን ስናጣ ከፍተኛ የቁጭት ስሜት በእያንዳንዳችን የቡድናችን ተጨዋቾች ውስጥ ስለነበር ከዛ ተነስተንም ነው ከዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታችን አንስቶ ዘንድሮ ይህን የሊግ ዋንጫ አስቀድመን ማንሳታችንን እናረጋግጣለን በሚል መርህ ቃል በመነሳት ለድሉ ልንበቃ የቻልነውና የአሸናፊነት መንፈሳችን እና ቁርጠኛ መሆናችንም ጭምር ነው ለስኬታማነታችን እንድንበቃ ያደረገን”፡፡

በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አነሳለው ብሎ አስቀድሞ አልሞ እንደነበር

“አዎን፤ የፋሲል ከነማ ተጨዋች ከሆንኩ በኋላ ነው ይህን ዋንጫ ከክለቡ ጋር ላገኝ እንደምችል አስቀድሜና እርግጠኛም ሆኔ ለማለም የቻልኩት፤ ምክንያቱም ፋሲል ከነማ ጠንካራ ቡድን ስለሆነና የጥሎ ማለፍና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫንም ስላነሳ የሊጉ ዋንጫ እንደሚቀረን ሁላችንም ተነጋገርን፤ ከዓመት በፊት በምን መልኩ ይህን ዋንጫ እንዳጣን ሁላችንም እናውቃለንና ወደ ስራና ስራ ብቻ ገባን፤ የዘንድሮ ኳስ ደግሞ ዲ.ኤስ.ቲቪ ያስተላለፈው በመሆኑ ለእኛ በጣም ጠቅሞናል፤ ኳስ ጨዋታ በዚህ መልኩ በቀጥታ ሲታይ መጥፎ ስራ ብዙ አይሰራም፤ ከዚህ በፊት የነበረት ውድድር ግን ችግሮች ስለነበሩበት እኛን ጎድቶናል፤ አሁን ጨዋታው በግልፅ ስለታየም እኛን ውድድሩ ለድል አብቅቶናል፤ ይህን ካልኩ አይቀር ኳሳችን በእዚህ መልኩ በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉም አንድ እርምጃ ወደፊት ከፍ እንድንልም አድርጎናል”፡፡

ለፋሲል ከነማ ዘንድሮ ስትጫወት ጠንከር ያለ ጉዳትን አስተናግደህ ነበር፤ በኋላ ላይ ወደ ሜዳ በመመለስ ለቡድንህ መጫወት ችለሃል

“በኳስ ሊያጋጥም የሚችልና ያልጠበቅኩትን ጉዳት ነበር በመጀመሪያው ዙር የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታችን ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ስንጫወት ላስተናግድ የቻልኩት፤ ሁሉንም ነገር ፈጣሪ የሚያዘው ነው፤ ያኔ ብጎዳም መልሶ ደግሞ ፈጣሪዬ ወደ መልካም ጤንነቱ መልሶኝ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ተዘጋጅቶ ከነበረው የሊጉ ውድድር አንስቶ በባህርዳር ከተማ ላይም ሆነ በሐዋሳ ላይም ለቡድኔ መጫወትን ችያለውና ለእዚህ ላበቃኝ አምላኬ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርብለታለው”፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም የደረሰበት ጉዳት ለረጅም ጊዜ ከኳሱ ጋር ያለያየኛል ብሎ አስቦ እንደሆነ

“አዎን፤ ለዛ ያደርሰኛል ብዬ በጣም ሰግቼ ነበር፤ ምክንያቱም በተጨዋችነት ዘመኔ ከዚህ ቀደም የብሽሽትም ሆነ የቁርጭምጭሚት ህመሞች አጋጥሞኝ የማያውቅና ሌሎችንም ጠንከር ያሉ ጉዳቶችን አስተናግጄ የማላውቅ በመሆኑ ነው፤ ልክ ጉዳቱ እንደደረሰብኝ በጣም ነው ያዘንኩት፤ በቃ ከኳሱ የወጣሁበትም መሰለኝ፤ ከዛ ነው ህክምናዬን 4 ኪሎ ወደሚገኘው ዳጉ ሆስፒታል ሄጄ የተሰበረውን ትከሻዬን ከተሰራው በኋላ የቡድናችን ፊዚዮቴራፒ ሽመልስ ደሳለኝ እንዲህ ያለ ጉዳት በኳስ የሚያጋጥም ነው፤ ጉዳትህም ቀላል ነው በሚልና ሌሎችንም ነገሮች እያነሳልኝ እኔን ትሪት እያደረገኝና ንግግሮቹም ሞራል እየሆነኝ ስለመጣ ከዛ በመነሳት ነው ወደ ጤንነቴ በመመለስ ለቡድኔ ለመጫወት የቻልኩት”፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም ጉዳቱ ሲደርስብህ ምክንያት ስለሆነው የሲዳማ ቡናው ተጨዋች

“በጨዋታው ላይ ግጭቱን ያደረሰብኝ ተጨዋች ማን እንደሆነ ፈፅሞ አላውቅም ነበር፤ በሁለተኛው ዙር ድሬዳዋ ላይ በድጋሚ ከእነሱ ጋር ስንጫወት ነው ተጨዋቹ ወደ እኔ መጥቶ ይቅርታ ጉዳቱን ያደረስኩብህ እኔ ነኝ፤ በተጎዳክበት ወቅት ስልክ እየደወልኩ ይቅርታ ልልህ ስል አታነሳም ነበር ብሎ ሲያናግረኝ ልጁ እንዳይረበሽም ብዬ አይዞን ይሄ በኳስ ዓለም የሚፈጠር ነገር ነው፤ አውቀህም ያደረግክው ነገር አይደለም ብዬው ይቅርታውን ልቀበለውና ለጥያቄውም ላመሰግነው ችያለሁ”፡፡

በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ፋሲል ከነማን በመጪው ዓመት በምን መልኩ እንደሚጠብቀው

“ፋሲል ከነማ አሁን ላይ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ የት ደረጃ ላይ መገኘት እንዳለበት እቅድን አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው፤ በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና የመሆን ራህዩ ከፊታችን ተቀምጧልና ለምን ይህን ድል ለማሳካት ቅድመ ዝግጅታችንን ለምን አሁን አንጀምርም ብለን ተነስተናል፤ ለእዚሁም ባለፉት ሁለት ዓመታቶች ካደረግናቸው የኢንተርናሽናል ውድድሮቻችን ተሳትፎም ብዙ ነገርን ተምረናልና እነዚህን ውጤቶች ወደምናስመዘግብበት አቋም ለመምጣት ጥረቶችን የምናደርግ ይሆናልና የመጪው ዘመን ተሳትፎአችንም የሚሆነው ከእዚህ በፊት የሀገራችን ቡድኖች ካስመዘገቡት ውጤት የተሻለ የሚባለውን ውጤትም ማምጣት ነው”፡፡

አንተ ለፋሲል ከነማ በመጪው ጊዜ

“ከዚህ ቀደም በነበረኝ የቡድኑ ተሳትፎ አበረታች የሚባል እንቅስቃሴን ለቡድኔ እያሳየውኝና ጥሩ የሚባል ግልጋሎትንም እየሰጠሁት ነበር፤ ዘንድሮ ግን በጉዳት ለብዙ ጨዋታዎች ከሜዳ ርቄ ነበርና በምፈልገው መልኩ ክለቤን ብዙ ለማገልገል አልቻልኩም፤ በአሁን ሰዓት ላይ ግን በመልካም ጤንነት ላይ ስለሆንኩ የበፊት አቋሜ ላይ መጥቼ በመጪው ጊዜ ክለቤን ፋሲል ከነማን በሀገር ውስጥ ተሳትፎም ሆነ በኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎ ላይ አንድ ስቴፕ ወደፊት እንዲጓዝ መርዳት እፈልጋለው”፡፡

ፋሲል ከነማን ምን ይለየዋል

“አሸናፊነቱና አንድነቱ፤ ከዛ ባሻገርም አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ከተለያዩ ክልሎችና ብሔረሰቦችም የመጡ ስለሆኑና በፍቅርም ተሳስረን የዘንድሮ ውጤት እንዲገኝ ያደረግን ስለሆንን ይሄ ለየት ያደርገናል”፡፡

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጨዋች የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ስለመሆኑ

“ኮከብ ተጨዋችነቱ ለአቡበከር ናስር ይገባዋል፤ የቡድናችን ተጨዋች ሽመክት ጉግሳም በእኔ እይታ ጥሩ ተፎካክሮታል፤ ከሽሜ ጋር አብሬው ልጫወት ብችልም የእኔ የቅድሚያ ምርጫ አቡበከር ነው፤ ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ዋንጫን አያንሳ እንጂ አቡበከር ከሁሉም ተጨዋቾች በተሻለ መልኩ ጥሩ የውድድር ዘመንን ያሳለፈ ነው፤ በዛ ላይ 29 ግቦችን አስቆጥሮ የሀገሪቱን ሪከርድ ሰባብሮታል፤ ከዛ ውጪም ይሄ ተጨዋች ይህን ሁሉ ገድል ሊፈፅም የቻለውም የተካበተ ልምድ ያለው አጥቂ ሳይሆን ገና ልምዶችን ለማግኘት እየጣረ ያለ ተጨዋች ስለሆነም ነው በእዚህ እድሜው ይህን ሁሉ ጎሎችን ሊያስቆጥር በመቻሉ ምርጫዬ ሊሆን የቻለው፤ በዛ ላይ አቡበከር ጓደኛዬም ስለሆነ ዓላ እንዲጠብቀውና ወደተሻለ ሊግ ደረጃም ሄዶ እንዲጫወት ምኞቴም ነው”፡፡

ስለ ትዳር ህይወቱና ባለቤቱን ሲገልፃት

“የትዳር ህይወቴን በጥሩ መልኩ እየመራሁት ነው፤ ከባለቤቴ ኤሪያ እንድሪስ ጋርም ከ3 ዓመት በፊት በፈፀምነው ጋብቻ ኒሂማን ሰይድና ነዋል ሰይድ የተባሉ የሁለት ዓመት ከ8 ወርና የ4 ወር ልጅን ልናፈራ ችለናል፤ ባለቤቴን በተመለከተ ከእኔ የኳስ ህይወት ጀርባ ብዙ ነገሮችን ያደረገችልኝ ነች፤ በተለይ ሳንጋባ በፊት ስለ ኳስ ተጨዋች ህይወትም ከቤተሰብ ርቀን እንደምንኖር ጭምር በሚገባ ታውቃለችና ለእኔ የምታደርግልኝ እገዛ ከፍተኛ ነው፤ በእዚሁ አጋጣሚም ላመሰግናት እፈልጋለው”፡፡

በመጨረሻ

“በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ እንድበቃ ብዙ ነገሮችን ያደረገልኝን ዓላን ለእሱ ከፍተኛ ምስጋና ይገባውና በቅድሚያ እሱን ለማመስገን እፈልጋለው፤ ሲቀጥል ቤተሰቦቼ እናትና አባቴ አሉ፤ ወንድሞቼና እህቶቼም መቼም አይረሱም፤ ባለቤቴም ሌላዋ ተጠቃሽ ናት፤ ከዛ ውጪ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችም ወደላይ ከፍ እንድንል አድርገዋልና ለእነሱም ጭምር ምስጋና ይገባቸዋል”፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website