“የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ለመሆን እንደ ፋሲል ከነማ ለሁሉም ቡድን እኩል ግምት ልሰጥ ይገባል”
“ለወላይታ ድቻ ብቻ ሳይሆን ለተመረጥኩበት የብሄራዊ ቡድንም ምርጥ ግልጋሎቴን ልሰጥ ተዘጋጅቻለው”
በረከት ወልዴ
ወላይታ ድቻ ካፈራቸው እና ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉም በጥሩ ችሎታው እያስመለከተን ካሉት ድንቅ የመሀል ሜዳ ተጨዋቾቾ መካከል አንዱ ነው፤ በረከት ወልዴ ይባላል። ለዚህ ቡድን ከተተኪው አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በመጫወት የወደፊቱ የአገራችን ብሄራዊ ቡድን ተስፈኛ ተጨዋች መሆኑንም እያስመሰከረም ይገኛል።
የወላይታ ድቻው አማካይ በረከት በመሀል ሜዳ ላይ ኳስን ለቡድን አጋር ጓደኞቹ በጥሩ ሁኔታ ከማቀበል በተጨማሪ ከባላጋራ ተጨዋቾች ላይ የሚነጥቅበትም መንገድ ጥሩ ሲሆን በአይድከምነቴ ተጨዋችነቱም ይታወቃል። ሌላው አልሸነፍ ባይነቱም ካለው ችሎታ በተጨማሪ የተለየም ያደርገዋል። በረከትን የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ከቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መጠናቀቅና ቆይታዎች በኋላ ከትናንት ወዲያ ሐሙስ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግሮት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶታል።
ሀትሪክ፦ እንኳን ደስ አለህ?
- ማሰታውቂያ -
በረከት፦ ለምኑ?
ሀትሪክ፦ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው ብሄራዊ ቡድን ስለተመረጥክ?
በረከት፦ በእሱማ በጣም ነው የተደሰትኩት። አመሰግናለው። እንኳን አብሮ ደስ ያለን ማለትም እፈልጋለው። ምክንያቱም ለእዚህ ብሄራዊ ቡድን የተመረጥኩት በሊጉ ካሉ ብዙ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች መሀል ልመረጥ በመቻሌም ነው። ይህ መመረጤም ለወደፊቱ የብሄራዊ ቡድን ምርጫ ትልቅ የሞራል ስንቅም ነው የሚሆነኝና ዕድሉን በአግባቡ ልጠቀምበት ተዘጋጅቻለው።
ሀትሪክ፦ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንስ /ዋልያዎቹ/ በቀጣይ ጊዜ የምትመረጥ ይመስልሃል?
በረከት፦ አዎን፤ ጥሩ አቋሜን በሜዳ ላይ እያሳየው በመምጣት በአጭር ጊዜያቶች ውስጥ እንደምመረጥ ለዚህ እርግጠኛነቴን ልገልፅልህ እወዳለው።
ሀትሪክ፦ ከዚህ በፊት ለሀገርህ ብሄራዊ ቡድን ወይንም ደግሞ የተተኪው ቡድን የመመረጥ ዕድሉን አግኝተህ ታውቃለህ?
በረከት፦ በ2011 ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው ብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ የቻልኩ ቢሆንም ይህን መመረጤን በክለቤ በኩል እኔ አልሰማውም ነበር። ወላይታ ድቻ አዲስ አበባ መጥቶ ልክ ከስዑል ሽረ ጋር ለመጫወት ወደ ሽሬ ሊሄድ በነበረበት ሰዓት ላይም ነበር መመረጤን ላውቅ ችዬ ጊዜው በማለፉ ዕድሉ ሊያመልጠኝ የቻለውና አሁን ላይ ይህን የመመረጥ ዕድሉን ድጋሚ ስላገኘው ተደስቻለው።
ሀትሪክ፦ አሁን ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ተመርጠሃል፤ ከአንተ ምን እንጠብቅ?
በረከት፦ በቅድሚያ እንኳን ለዚህ ቡድን ተመረጥኩ። ከዚህ በኋላ በሚኖረኝ የኳስ ጉዞዬ ደግሞ ሀገሬን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በምርጥ ብቃት የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አለኝና ለወላይታ ዲቻ እንደምሰጠው ጥቅም ነው ለሀገሬም ከፍ ባለ ደረጃ ላይ ተገኝቼም ውጤታማ ብቃቴን መስጠት የምፈልገው።
ሀትሪክ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በረከት የውድድር ዘመኑን በምን መልኩ አሳለፈ?
በረከት፦ በምርጥና ደስ በሚል ሁኔታ ነው ዓመቱን ያሳለፍኩት። ከዚህ ቀደም ኳስን ዝም ብለን ጭምር ነበር የምንጫወተው። አሁን ግን ዲ ኤስ ቲ ቪ እያንዳንዱን ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት ያስተላልፍ ስለነበርና እነዚህን ግጥሚያዎች ደግሞ መላው ዓለም የሚከታተልበት ሁኔታም ስለተፈጠረ ያለንን ችሎታ ለማሳየት የቻልንበትም አጋጣሚ ስለነበር ጥሩ የውድድር ዓመትን ነው ያሳለፍኩበት።
ሀትሪክ፦ ዘንድሮ በምርጥ ብቃት ላይ ነው የምትገኘው?
በረከት፦ ከዚህ በላይ ገና እጓዛለው፤ ያሰብኩበት ደረጃ ላይም ገና አልደረስኩም።
የሚቀሩኝ ነገሮች አሉ። በእነሱ ሙሉ ስሆን የእኔን ሙሉ አቅም የምትመለከቱት ነው የሚሆነው።
ሀትሪክ፦ ወላይታ ዲቻስ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የዘኔድሮ ተሳትፎ እንዴት ነበር?
በረከት፦ ክለባችንን እንዳያችሁት የመጀመሪያው ዙር አካባቢ በኳሱ ጥሩ ልንሆን ብንችልም ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ግን ችግር ላይ ነበር። የሁለተኛው ዙር ላይ ግን አዲስ አሰልጣኝ ወደ ቡድናችን ሲመጣና እኛን ሊጠቅሙን የሚችሉም ሲኒየር ተጨዋቾች ወደ ቡድናችን ሲመጡ በብዙ ነገሮች ልንቀየር ቻልንና ጥሩ ውጤትን ልናስመዘግብ ቻልን። ወላይታ ዲቻ ብዙ ጊዜ በመውረድና አለመውረድ ዞን ውስጥ የሚዳክር ቡድን ነበር። ዘንድሮ ግን ያውም ብዙ ችግሮችን አሳልፎ 13 ክለቦች ብቻ በተሳተፉበትና ያውም ከባድ በነበረው የሊጉ ውድድር ላይ የስምንተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ በጥሩ ውጤት የሚገለፅለት ነው።
ሀትሪክ፦ በዘንድሮ ተሳትፎአችሁ ከዚህ የተሻለ ውጤትን ማስመዝገብ ትችሉ ነበር?
በረከት፦ አዎን። እስከ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ሆነን ውድድሩን ማጠናቀቅ እንችል ነበር። ያም ሆኖ ግን ኮቪድ የእኛን ክለብ ጎብኝቶት ነበርና ያ ወረርሽኝ በአንድ አንድ ጨዋታዎቻችን ላይ ነጥብ እንድንጥል አድርጎን ውጤታችንን ወደ ላይ እንዳንሰቅለው ቢያደርገንም ከሞላ ጎደል ግን ውጤታችን ጥሩ የሚባል ነው።
ሀትሪክ፦ አቡበከር ናስር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ ተጨዋቾች ሽልማትን ተቆጣጥሮ ወስዷል፤ ይህን ስታውቅ እንደ ወላይታ ዲቻ ተጨዋችነትህ ምን አልክ?
በረከት፦ ሽልማቶቹ ለአቡበከር ይገባዋል። ዘንድሮ እሱ በጣም ለፍቷል፤ በሊጉ ጎልቶም ታይቷል። ከዛ በተጨማሪም የተለያዩ ሪከርዶችንም ሰብሯል። ሁሉንም ባሳመነ መልኩም የጥረቱንም ነው ያገኘውና ሽልማቱ ሁላችንንም የሊጉን ተጨዋቾች ያስማማም ነው።
ሀትሪክ፦ የእነ አቡበከርን መሸለም ስታይ እኔስ የሚል ስሜት አልተሰማህም?
በረከት፦ ይሰማኛል እንጂ። የእሱ መሸለም ለነገ ለእኔም ሆነ ለሌሎች ተጨዋቾች ብርታት ነው የሚሆነንና ከእሱ ብዙ ነገርን እንማራለን።
ሀትሪክ፦ ወንድማገኝ ሀይሉም በተስፋ ሰጪ ተጨዋችነት ከሐዋሳ ከተማ ክለብ በመመረጥ ተሸልሟል?
በረከት፦ ይሄ አይነት ሽልማት በሊጉ ያልተለመደ ነበርና ወጣት ተጨዋቾችን ማበረታታት ጥሩ ነው። ይህ ሽልማትም ነገ በርካታ ወጣት ተጨዋቾች በሊጉ ላይ ጎልተው እንዲወጡም ያደርጋል።
ሀትሪክ፦ ፋሲል ከነማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቷል፤ የእነሱን ሻምፒዮናነት እንዴት ተመለከትከው?
በረከት፦ ፋሲል ከነማ በመጀመሪያ ደረጃ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው በጣም ጠንካራ ቡድን ስለሆነ ነው። ብዙ ጨዋታዎችን በማሸነፍም ነው ባለድል የሆነው። ከዛም በተጨማሪ ለሁሉም ቡድኖችም እኩል ግምትን ሰጥቶም ወደ ሜዳ ስለገባ ያ ጠቅሞትም ነው የድሉ ባለቤት ለመሆን የቻለውና ስኬቱ በትክክል የሚገባው ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ሀትሪክ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ጠንካራ ውድድር ነበር?
በረከት፦ ለእኔ አዎን። ምክንያቱም በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ግጥሚያዎችን በቀላሉ አታሸንፍምና ከዛም በተጨማሪ ጨዋታዎቹ ሁሉ በዲ ኤስ ቲቪ ስለሚተላለፉና አንተም ራስህን ለማሳየት ስለምትጥር እንደዚሁም ደግሞ ኳስ መቻልም ወሳኝነት ስላለውና የጨዋታዎቹም በቀጥታ ስርጭት መተላለፋቸውን ስታይ ብሄራዊ ቡድናችንንም አሪፍ አድርጎታልና የቤትኪንጉ የዘንድሮ ውድድር በጠንካራነቱ የሚገለፅ ነው።
ሀትሪክ፦ በረከት የዝውውር መስኮቱ ሲጠናቀቅ ወደ አንድ የሀገሪቱ ትልቅ ቡድን ሊዘዋወር ነው እየተባለ ነው?
በረከት፦ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አሁን ላይ የማውቀው ነገር የለም። ሰኔ 30 ሲያልቅ ግን ሁሉንም ነገር አሳውቃለው።
ሀትሪክ፦ የበረከት ህልም?
በረከት፦ በኳሱ ከሀገር ወጥቼ እስከ ባህርማዶ ድረስ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ዘልቄ መጫወትን አልማለው። ያን ዕድል ለማግኘትም ጠንክሬ እሰራለው።
ሀትሪክ፦ ከባህርማዶ ቡድኖች የማን ደጋፊ ነህ?
በረከት፦ የማንቸስተር ዩናይትድ።
ሀትሪክ፦ በብሄራዊ ቡድን ደረጃስ?
በረከት፦ ከሀገሬ ውጪ የብራዚልና የፈረንሳይ ደጋፊ ነኝ።
ሀትሪክ፦ ከምግብ ቀዳሚው ምርጫ?
በረከት፦ አልመርጥም። ሁሉንም እበላለው።
ሀትሪክ፦ ከመጠጥ?
በረከት፦ ውሃ።
ሀትሪክ፦ ከሙዚቃ?
በረከት፦ መዝሙርን ነው የማዳምጠው።
ሀትሪክ፦ በመጨረሻ?
በረከት፦ በእግር ኳሱ እዚህ ደረጃ ያደረሰኝን ፈጣሪዬን በቅድሚያ ማመስገን እፈልጋለው። ሲቀጥል ደግሞ ቤተሰቦቼንና ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች በተለይ ደግሞ ከጸጣሪ በታች እንደ አባቴ የማየውን ዘነበ ፍስሃን ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ ብዙ ነገሮችን አሳይቶኛልና ይመስገንልኝ። ከእሱ ውጪ ደግሞ እንደ መሳይ ተፈሪ ያሉ ሌሎችም አሰልጣኞች አሉና እነሱንና የወላይታ ዲቻን ደጋፊዎች ላመሰግናቸው እወዳለውኝ።