“የድሬደዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ቀጣዮቹ 2 ጨዋታዎች ድረስ እንዲታገሰኝ እፈልግ ነበር ነገር ግን አልተሳካም በዚህም ቅር ብሎኛል” ሲል ተሰናባቹ አሰልጣኝ ፍሰሃ ጥዑመልሳን ገለፁ፡፡ አሰልጣኙ በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፁት “በውጫዊ ምክንያቶች ያጣኋቸው ውጤቶች ጎድተውኛል ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ዳኛው ፍፁም ቅጣት ምት ከልክሎኛል ግብ የማስቆጠር እድል አግኝተን በአንግሉ ተመልሶብናል፤ ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ባገኝ ከወራጅ ቀጠና ወጥተን 8ኛ ደረጃ ላይ እንሆን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኙ ሲናገሩ “ቦርዱ እድል ሊሰጠኝ ይገባ ነበር በቀጣይ የምንገጥመው ሀዋሳ ከተማና ሰበታ ከተማን ነው ሁለቱን ስናሸንፍ ቡድናችን የሚመጣው ስድስተኛ ደረጃ ላይ ነው ለዚህ እድል ቢሰጡኝ ደስ ይለኝ ነበር ነገር ግን ባለመሆኑ አዝኛለሁ ቀጣይ የሚመጣው አሰልጣኝ ሀዋሳ ከተማና ሰበታ ከተማን ካሸነፈ መጣና ቡድኑን ከጉድ አወጣው ሊባል ነው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አሰልጣኝ ፍሰሃ ጥዑመልሳን “አንድ አሰልጣኝ ቡድኑ ውጤት እስከሌለው ድረስ ጥሩ ሰራ አልሰራ መሰናበቱ አይቀሬ ነው ጊዜው ወደ ላይ አንጋጥ የሚባልበት ነው ቡድኔ ተስፋ ያለው ነው ውጤቱ ቢበላሽም ባለሙያዎች የሰራሁትን ስለሚያዩና ስለሚረዱ በቀጣይ ሌላ ስራ መገኘቱ አይቀርም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ባለፉት 4 አመታት ከክለቡ ጋር ነበርኩ አራቱን አመት ሙሉ የምንጫወተው ላለመውረድ ነው አሁንም የተለየ ነገር የለም ቢታገሱኝ ደስ ይለኝ ነበር አልሆነም ለቡድኑ አባላት መልካም ውጤት እመኛለሁ በይፋ ባያሰናብቱኝም ካሁን በኋላ ወደ ክለቡ አልመለስም” ያሉት አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን “በሚዲያ የምናገረው ትኩረት እንዳሰበ አውቃለሁ፡፡ ትኩረት ለመሳብ ብዬ ሳይሆን የመጣልኝ ፊት ለፊት የምናገረው የድሬደዋ ሰው ስለሆንኩ ነው የሚሰማኝን ተንፍሼ በሠላም አድራለሁ” ሲሉ ለሀትሪክ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የድሬደዋ ከተማ እግር ኳስ ቡድን የቦርድ አባላት አሰልጣኝ ፍሰሀን በአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ በመተካት እስከ ሰኔ 30/2014 ድረስ ያለውን የኮንትራት ቅጥር ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ድሬደዋ በእስካሁኑ 11 ጨዋታዎች 10 ነጥብና 5 የግብ እዳ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሰልጣኝ ዘማርያም ቡድኑን ይዞ እየመራ በ13ኛው ሳምንት መርሃ ግብር የካቲት 18/2013 ከሙሉጌታ ምህረት ሀዋሳ ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የአሰልጣኝነቱን ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አስተያየት ይስጡ