በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተጠባቂውን ጨዋታ ማን በድል ይወጣል?

በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተጠባቂውን ጨዋታ ማን በድል ይወጣል?

ሀዲያ ሆሳዕና ወይንስ ፋሲል ከነማ?
“ለፋሲሎች ብቻ ብለን አልተዘጋጀንም፤ እነሱን አሸንፈን መሪነታችንን እናጠናክራለን”
አማኑኤል ጎበና /ሀዲያ ሆሳዕና/

“ለጠንካራው ሀዲያ በሚመጥን መልኩ ስለተዘጋጀን አሸንፈናቸው መሪነቱን እንነጥቃቸዋለን”
እንየው ካሳሁን /ፋሲል ከነማ/


ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እስከ 6ኛ ሳምንት የነበረውን የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን አጠናቆ አሁን ላይ ደግሞ ተራውን ለጅማ ከተማ በማስረከብ ከትናንት ዕለት አንስቶ በጅማ ዩንቨርሲቲ እግር ኳስ ሜዳ ላይ ጨዋታዎቹን ማድረግ ጀምሯል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ጅማ ከተማ የተዘዋወረው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እነዚህ ቀጣይ ጨዋታዎችም በትናንትናው ዕለት ሲጀመር ባለሜዳዎቹን ጅማ አባጅፋርን እና ቅ/ጊዮርጊስን ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውንም በጌታነህ ከበደ ሶስት ግቦች እንግዳው ቡድን ቅ/ጊዮርጊስ 3-2 በሆነ ውጤት ሊያሸንፍም ችሏል፤ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ትናንትም አሰልጣኙን ደለለኝ ደቻሳን እና ረዳቱን ባሰናበተው በወላይታ ድቻ እና በሰበታ ከተማ መካከል ግጥሚያ የተደረገ ሲሆን ይኸው ውድድር ዛሬም ይቀጥልና ከቀኑ 4፡00 ሰዓት ባህር ዳር ከተማን ከሐዋሳ ከተማ እንደዚሁም ደግሞ በ9፡00 ሰዓት ሲዳማ ቡናን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያገናኛል፡፡

የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የእዚህ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ሊጉን እየመራ ባለው በሀዲያ ሆሳዕናና በፋሲል ከነማ ክለቦች መካከል የሚደረግ ሲሆን ይህን ጨዋታ በተመለከተ የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ምን ሊመስል እንደሚችል እና ስለቡድናቸው አቋም እንደዚሁም ደግሞ በእዚሀ ተጠበቂ ጨዋታ ስለሚመዘገበው ውጤት ከሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ ለሀዲያ ሆሳዕናው የመሀል ሜዳ ተጨዋች አማኑኤል ጎበናና ለፋሲል ከነማው የግራ መስመር የኮሪደር ስፍራው ተጨዋች እንየው ካሳሁን የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጥያቄዎችን አቅርቦላቸዋል፤ እነሱም ምላሽን ሰጥተውታል፡፡

በሀዲያ ሆሳዕና እና በፋሲል ከነማ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ምን መልክ ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ? ለጨዋታው በምን መልኩስ እየተዘጋጃችሁ ነው? ማንስ የጨዋታው አሸናፊ ይሆናል? ግጥሚያውስ በጣም ተጠባቂ ነው ማለት ይቻላል…? ለሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ አማኑኤል ሲመልስ “ከፋሲል ከነማ ጋር ለሚኖረን የ7ኛው ሳምንት ጨዋታ ቡድናችን እየተዘጋጀ ያለው ለማንም ተጋጣሚው በሚሰጠው አይነት ግምት እንጂ ለእነሱ ብለን ብቻ በተለየ መልኩ የተዘጋጀንበት ሁኔታ የለም፤ ፋሲል ከነማ በሊጉ ጠንካራ እና ጥሩ ቡድን ነው፤ የውድድሩን ዋንጫ ለማንሳት ሲልም ሊጉን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮም በመፎካከር ላይ የሚገኝም ቡድን ነው፤ ከዛ ባሻገር በያዛቸው የተጨዋቾች ስብስቡም ውጤትን መቀየር የሚችሉ ብዙ ልጆችም አሉት፤ ይሄ ሲታይና እኛ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በዘንድሮው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችን ላይ ጥንካሬያችንን በማስመስከር እና የሊጉን ውድድርም እስከመምራት ደረጃም ላይ የተገኘን በመሆናችን በጣም ተጠባቂ ነው የምንለውን እና የምንረዳውን የነገውን ጨዋታችንን በእኛ አሸናፊነት በማጠናቀቅ መሪነታችንን ልንጠናክርበት ተዘጋጅተናል” ብሏል፡፡ የፋሲል ከነማው ተጨዋች እንየው ካሳሁን ደግሞ በእዚህ ጥያቄ ዙሪያ ምላሹን ሲሰጥ “የሀዲያ ሆሳዕና እና የእኛ ፋሲሎች የነገው ጨዋታ ተጋጣሚያችን በአሁን ሰዓት ላይ እያስመዘገበው ካለው ውጤት፤ ጠንካራነቱንም በየጨዋታው እያሳየ ከመሆኑና ሊጉንም ከመምራቱ አኳያ ግጥሚያው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቅ ነው፤ ለእዚህ ትልቅ ጨዋታም አስቀድመን ጅማ ከተማም በመግባት በበቂ ሁኔታ ዝግጅታችንን አድርገናል፤ ለእነሱ አቅምና ችሎታ በሚመጥን ሁኔታም ነው ልምምዳችንን ስንሰራ እና ስንዘጋጅም የነበርነው፤ ይኸውን ጨዋታ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነን ስለምናደርግ እና ግጥሚያው ደግሞ በጣም ተጠባቂ እና በመሪነት ደረጃም ላይ ሊያስቀምጠን የሚችል ጨዋታም እንደሆነ ስለምናውቅ ለጠንካራው ሀዲያ በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀው ቡድናችን የነገውን ጨዋታ በማሸነፍ የሊጉን መሪነት እንደምንነጥቃቸው እርግጠኛ ነኝ” ሲል መልሱን ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሀዲያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ በአሁን ሰዓት ላይ ስላላቸው ወቅታዊ አቋም የተጠየቁት ሁለቱ ተጨዋቾች ምላሻችሁን ስጡ ሲባሉም አማኑኤል ይሄን ብሏል “ሀዲያ በአሁን ሰዓት ላይ ያለው አቋም ጥሩ እና ሁላችንንም ደስተኛ ያደረገን ነው፤ እያንዳንዱን ጨዋታ በህብረት በማጥቃት እና በመከላከል እንደ ቡድን በመጫወትም በሊጉ መልካም ጅማሬን እያደረገን ውድድሩን እየመራንም ነው የምንገኘው፤ ሌላው ለጨዋታ ያለን ከፍተኛ ተነሳሽነታችንና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናችንም ከፍ ያለ ስለሆነ ይሄን በማስቀጠል ዘንድሮ ምርጥ የሚባል ውጤትን እናስመዘግባለን” ብሏል፡፡ የፋሲል ከነማው እንየው ካሳሁንም በእዚህ ዙሪያ የሰጠው ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል “ፋሲል ከነማ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ራሱን በማሻሻል የመጣ ቡድን ነው፤ ባለፉት ስድስት ግጥሚያዎቹም ውጤት ባስመዘገበባቸውም ሆነ ነጥብ ባጣባቸው ጨዋታዎች ላይ የነበሩበትን ክፍተቶች ከኮቺንግ ስታፉ ጋር በመነጋገር እያረማቸው የሄደና ወደ አሸናፊነት መንፈሱም በፍጥነት የመጣ ስለሆነ በእዚህ ሁኔታ ላይ መገኘታችን ሁላችንንም አስደስቶናል፤ ፋሲል ከነማ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ማንም ያውቃል፤ በዘንድሮ የውድድር ዘመንም ይሄ ሙሉ ጥንካሬው ከውጤት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ጭምር ሊመጣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘጋጀ ይገኛልና ያን ጥንካሬያችንን አሳይተን ነው የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የምንፈልገው”፡፡

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor