“የእኔ የመጀመሪያ እቅዴና ግቤ በወጣት ተጨዋቾች የተገነባ ጠንካራ ቡድንን መስራት ነው” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት

“በሐዋሳ የአሰልጣኝነት ቆይታዬ በአንዴ ተነስቼ ውጤት አመጣለው አልልም”

“የእኔ የመጀመሪያ እቅዴና ግቤ በወጣት ተጨዋቾች የተገነባ ጠንካራ ቡድንን መስራት ነው”
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት


በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ላይ ከተጫወተባቸው ክለቦቹ ሐዋሳ ከተማ፣ ቅ/ጊዮርጊስ እና ደደቢት ቡድኖች ጋር የሊጉንና የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት የቻለው ሙሉጌታ ምህረት በአሰልጣኝነት ዘመኑ ደግሞ እንደተጨዋችነቱ ጊዜ ሁሉ የተለያዩ የድል ስኬቶችን ለመጎናፀፍ እቅድ መያዙን ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የእግር ኳስ ተጨዋች እያለ ከሐዋሳ ከተማ እና ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር የፕሪምየር ሊጉን እንደዚሁም ደግሞ ከደደቢት ጋር የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ለማንሳት የቻለው ሙሉጌታ የአሁን ሰዓት ላይ ሐዋሳን በአሰልጣኝነት ለመምራት ለተረከበው የኃላፊነቱ ቦታ ብቁ መሆኑንም ከጋዜጣው ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ቡድኑን በኃላፊነት ለመምራት ከተዘጋጀው ሙሉጌታ ምህረት ጋር የዝግጅት ክፍላችን ያደረገው አጠር ያለ ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ካበቃ በኋላ በቀጥታ ወደ አሰልጣኝነቱ ሙያ ነበር የተሰማራኸው፤ ወዲያው የማሰልጠን ፍላጎቱ ነበረህ ማለት ነው?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- አዎን፤ ለዛም ነው እየተጫወትኩም የአሰልጣኝነት ኮርሱን የወሰድኩት፤ በኋላም ላይ በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔ ለብዙ ዓመታቶች መጫወቴን ያውቅ የነበረው አሰልጣኝ ውበቱ አባተምየሐዋሳ ከተማ ክለብን በተረከበበት ሰዓት ላይ እኔ ኳስ አቁሜ ስለነበር የእሱ ረዳት እንድሆንና አብረንም እንድንሰራሲጠራኝ እኔም ዓይኔን ሳላሽና ለረጅም ዓመታትም የተጫወትኩበትን ክለብ ማገልገል አለብኝም በሚል ውሳኔዬየእሱን ጥሪ ተቀብዬ አብሬው መስራት ጀመርኩ፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው /ሞውሪኖ/ ተጨዋች በነበርክበት ሰዓት ወደፊት ኳስ ስታቆም አሰልጣኝ ለመሆን እንደምትችል እና ለዛም መዘጋጀት እንዳለብህ ተንብዮ ነበር ይባላል?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- የእውነት ነው፤ እሱ ኳስን ከምንጫወትበት ዘመን አንስቶ ነው በተሰማራንበት ሙያ እንድናድግ ይፈልግስለነበር ኳስን እየተጫወትን በነበርንበት ሰዓት ነው የአሰልጣኝነት ኮርስ ሲመጣ ውሰዱ ይል የነበረው፤ በተለይ ደግሞ በእኔ ላይ ወደፊት አሰልጣኝ ለመሆን እንደምችል የተመለከታቸው ጥሩ ጥሩ ነገሮች ስለነበሩ አንተ ኳስ ስታቆም አሰልጣኝ መሆን አለብህ፤ ጥሩ አሰልጣኝ ለመሆንም ትችላለህ ስለሚለኝ በእሱ ግፊት ነው ወደ ዛሬው የአሰልጣኝነት ሙያው ላይ ለማምራት የቻልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ሐዋሳ ከተማዎች የዋናው ቡድን የማሰልጠን ኃላፊነቱን እንዴት ሊሰጡህ ቻሉ? ለእዚህ ቦታስ አሁን ላይ ራስህን ብቁ አሰልጣኝ አድርገህ ነው የምታስበው?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- አዎን፤ በሚገባ፤ እነሱ ይህን ሀላፊነት ለእኔ ከመስጠታቸው በፊት በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ረዳት ሆኜ እየሰራው ነበር፤ ከዛም ነው ምን እንደተፈጠረ ባላወቅኩበት ሁኔታ የአካባቢው የስፖርት ቤተሰብን ጨምሮ ስፖርቱን በቅርቡ ጠንቅቀው የሚያውቁት የክለቡ ሰዎች በተጨዋችነት ዘመኔ ያለኝን የመጫወት ልምድ እና በተለያዩ አሰልጣኞችም የሰለጠንኩ በመሆኑ ከዛም ባሻገር ደግሞ ወደ ማሰልጠኑም ሙያ ከመጣው በኋላ የተለያዩ የሀገራችን አሰልጣኞች ረዳት አሰልጣኝ ሆኜም በመስራቴና በዛ ውስጥም የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን በሚያክል ደረጃም ረዳት ሆኜም ስለሰራው ከዛ በመነሳት ነው ሹመቱን ለእኔሊያፀድቁልኝ የቻሉት፤ ከዛ ውሳኔ ላይ ከደረሱም በኋላ ለበርካታ ዓመታት የተጫወትኩበትን የቀድሞ ክለቤን ማገልገል አለብኝ በሚልም ውሳኔያቸውን ወዲያው ተቀበልኩ፤ ሐዋሳ ከተማን ለማሰልጠን አሁን ላይ የመጣሁበት ጊዜ ትክክለኛው ሰዓት ላይ ነው፤ ቡድኑን የማሰልጠን ብቃቱም አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በአሰልጣኝነት ሙያህ አሁን ላይ ራስህን ለማሻሻል እና ለማሳደግ ምን አይነት ጥረቶችን እያደረግህ ነው?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- የእግር ኳስ አሰልጣኝ ስትሆን የስልጠና ኮርሶችንመውሰድ እና ማሰልጠን ብቻ አንተን በሙያው ብቃትህ ላይ ያሳድግሃል ብዬ ፈፅሞ ስለማላስብ በአሁን ሰዓት ራሴን እያዘጋጀው ያለሁት የተለያዩ ኮርሶችን ከመውሰድ ባሻገር ከትላልቅ የሀገሪቱ ባለሙያዎች ጋርም ጠጋ ጠጋ ብዬ ከእነሱ ብዙ ልምዶችን በመቅሰም እና ከዛ ውጪም የተለያዩ የስልጠና ዶክመንቶችንም በመውሰድ እንደዚሁም ከእዚህ በኋላምየአሰልጣኝነት ሙያው እየከበደ ስለሚሄድም ሁሌም በማንበብ እና አሁን ላይ ደግሞ ጊዜው የቴክኖሎጂም ስለሆነና ለኮምፒውተርም ቅርብ ስለሆንኩ ራሴን በስልጠናው ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረትን እያደረግኩ ነው፤ ሌላው ራሴን በሙያዬ ለማሻሻል እና ለመለወጥ በማደርገው ጥረትም ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም እኔን ለመርዳት ፈቃደኛ ስለሆኑም እሳቸውን ሳላመሰግናቸው አላልፍም፡፡

ሀትሪክ፡- በሐዋሳ ከተማ የውበቱ አባተ ረዳት ሆነህ ስትሰራ ለእሱ ታማኝ አሰልጣኝ ሆነህ ነበር የቀረብከው? እንደ ረዳትነትህስ ሙያዊ እገዛንስታደርግለት ነበር?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- አዎን፤ በምችለው አቅምና በማውቀው ሁኔታያኔ ለውበቱ አንድአንድ ሀሳቦችን አቀርብለት ነበር፤ ብዙ ጊዜ ረዳት አሰልጣኝ ሆነህ ስትሰራ ብዙ ነገሮችን የምትማረው ከዋናው አሰልጣኝ ነው፤ አንተም ደግሞ በምትችለው አቅም አሰልጣኝህን የምታግዝበትም ሁኔታ ነበርና የእሱ ታማኝ ሆኜም ነበር ስሰራ የነበረው፤ ከዛ ውጪም እኔም ከውበቱ የተማርኳቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ ከእነዚህ በመነሳት ለወደፊቱ አሰልጣኝነቴም የራሴን ነገሮች በማንፀባረቅ ጭምር ጥሩ ነገሮችን በሙያዬ ኃላፊነት እሰራለሁ ብዬ አስባለሁኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ሐዋሳ ከተማን በተጨዋችነት ዘመንህ የፕሪምየር ሊጉና የጥሎ ማለፉ ሻምፒዮና አድርግሃል፤ በአሰልጣኝነት ሙያህስ አሁን ላይ ይህን ድል የምታሳካ ይመስልሃል?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- አንድ ቡድንን ስትሰራ ውጤት ለማምጣት ጊዜ ያስፈልጋል፤ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ በሀላፊነት የተረከብኩትን ሀዋሳ ከተማን ለማሰልጠን ስዘጋጅ ይህን የስኬት ድል እቀዳጃለሁ ብዬ የማስበው ያኔ ነው፤ ያለበለዚያ ግን ውጤት እኮ በአጋጣሚም ሊመጣ ይችላልና በኋላ ላይ ያ ውጤት ዘላቂነት ከሌለውና ሻምፒዮና ከሆንክበት ዓመታቶች በኋላ ላለመውረድ የምትጫወትበት ከሆነ ያ አንተ ላይ ከባድ ነገርን ነው ሊፈጥርብህ የሚችለው፤ ስለዚህምይህን ስለማውቅ የሐዋሳ ከተማ ክለብን በኃላፊነት በተረከብኩበት የዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ በአንዴ ከመሬት ተነስቼ ይህን የድል ውጤት አመጣለው ብዬ ፈፅሞ አልናገርም፤ ሐዋሳን ሳሰለጥን የእኔ የመጀመሪያ እቅዴና ግቤ ብቁ የሆኑ ተጨዋቾችን ማፍራት እና በወጣት ተጨዋቾችም የተገነባ ጠንካራ እና ዘላቂ የሆነ ቡድንን መስራት ነው፡፡ ከዛም በኋላ ደግሞ የስኬት ውጤትን ለማምጣትጊዜ ያስፈልግሃልና የተሰጠህን ጊዜ ተጠቅመህ ለክለቡ ውጤት ልታመጣለት ይገባልና በዛ ደረጃ ነው ስራን ልትሰራ የሚገባው፡፡

ሀትሪክ፡- ሐዋሳ ከተማን በምን መልኩ ልትገነባው እና ምን አይነት ቅርፅ ያለው ቡድን ልታደርገው ተዘጋጅተሃል? የክለባችሁ ተጨዋች መስፍንስ አሁን ላይ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራን ከማድረጉና ከእናንተም ጋር ካለመሆኑ አኳያ ካልተቀላቀላችሁ ይጎዳችሁ እንደሆነ….?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- ሐዋሳ ከተማን በውድድር ዘመኑ ይዤ ለመቅረብ የተዘጋጀሁት ጠንካራና በወጣቶች የተገነባም ቡድን አድርጌ ነው፤ ብዙም የጨመርኳቸው ተጨዋቾች የሉም፤ በአብዛኛው ያሉትን ተጨዋቾችም ነው ያስቀጠልኩትና ይህን ቡድን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የራሱ የሆነ ቅርፅ ያለው ቡድን አድርጌ ለማቅረብ ተዘጋጅቻለሁ፤ መስፍንን በሚመለከት የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት የሙከራ ዕድሉን በማግኘቱ ሁላችንም ደስ ብሎናል፤ ይህ ተጨዋች በክለባችን ገና የሁለት ዓመት ውል ያለው ነው፤ ጥቅሙ ለእሱም ለክለባችንም ስለሆነ በሙከራው ጊዜ እንዲሳካለትም እንፈልጋለን፤ እሱ ያን እድል አገኘ ማለት ደግሞ ለሌሎች በርካታ ወጣት ተጨዋቾቻችን ቦታ እንዲኖራቸው እና ነገም እነሱ እንደ እሱ ይህን እድል ለማግኘት በርትተው ስለሚሰሩ እና ለክለባቸውም ጥሩ ውጤት ለማምጣት ስለሚጥሩ ይሄን በጥሩ አጋጣሚነትም ነው እየተመለከትነው የምንገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ ወረርሽኝ ርቀን ከነበርንበት እግር ኳሳችን ዳግም ልንመለስ ተቃርበናል፤ በእዚህ ምን ስሜት ተፈጠረብህ?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- ይሄ ለመሆን በመቻሉ በጣም ደስ ይላል፤ ምክንያቱም በኮቪድ እግር ኳሱ ሲቋረጥ ተጨዋቾችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚወዱት እና ራሳቸውን ዘና ከሚያደርጉት እንደዚሁም ደግሞ ከሌሎች ተመሳሳይ ከሆኑም ነገሮች ነበር የራቁትና በብዙ ነገር ተቸግረው ነበር፤ አሁን ግን እግር ኳሱ እንዲጀመር ሲፈቀድ ሰውም ስፖርትን ሰርቶ ራሱን እንዲያነቃቃ የሚያስችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ስፖርቱ የተመለሰበት ሁኔታ ደግሞ ህግን በአማከለ መልኩ መሆኑም ማለትም ሰው ራሱን ከኮቪድ በሚከላከልበት ያለ ተመልካች ሊጉ ሊካሄድ ያለበት ሁኔታም ተገቢ ነው፤ ከጊዜያቶች በኋላ ግን በተመልካች የምንጫወትበት ሁኔታመው ስለሚመጣ እሱንም መጠበቅ ይገባናል፡፡

ሀትሪክ፡- ሊቨርፑልን እንደምትደግፍ እናውቃለን፤ ዘንድሮ ባሳካው የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ በጣም ተደሰትክ?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- ከምገልፅልህ በላይ ነዋ! ምክንያቱም የእዚህ ቡድን እና የስቴቨን ጄራርድ ዋንጫ ማግኘት የሁልጊዜም እልሜና ፍላጎቴም ነበርና፤ ጄራርድ ለእዚህ ድል ባይበቃም ወደ አሰልጣኝነት በመምጣቱ እና ሊቨርፑል ደግሞ ይህን ዋንጫ ስላገኘ በጣም ደስ ብሎኛል፤ የክለቡ ምርጥነት ደግሞ አሁንም ይቀጥላል፤ ከዛ ውጪ ይሄ ቡድን አሁን ላይ ጺ㝕ጎ አልካንትራን መጨመሩም ይበልጥ ደስ ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የሊቨርፑል ጨዋታን የምትመልክትበት የራስህ የሆነ መንገድ አለህ?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- አዎን፤ ብዙ ጊዜ ደስታዬን መግለፅ አልችልም፤ ኳስ የማየውም ለብቻዬ ነው፤ በተለይ ቤት ውስጥ በምመለከትበት ሰዓት ባለቤቴንና ልጄንም ከሳሎን በማስወጣት ነው ብቻዬንም የምመለከተው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…. ?

አሰልጣኝ ሙሉጌታ፡- የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በእኔ ላይ እምነትን ጥሎ ትልቁን ኃላፊነት ስለሰጠኝ ከልብ አመሰግናለው፤ ከዛ ውጪም ረዳት አሰልጣኝ ሆኜ በሰራሁባቸው ጊዜያቶች በብሄራዊ ቡድን በኢንስትራክተር አብርሃም እንደዚሁም በክለብ ደረጃ በውበቱ አባተ ስር ሆኜ ያውቅኳቸው ነገሮች ስላሉ ለእነሱ የሙያ እገዛ ምስጋናን እያቀረብኩ በጊዜ ሂደት ይሄን ቡድኔን ለጠንካራ ተፎካካሪነትና ከዓመታት በኋላ ደግሞ ሻምፒዮና ለማድረግ ጠንክሬ እሰራለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website