ሀድያ ሆሳዕና ወሳኝ ተጨዋቾቹን ሊያጣ ነው


ሀዲያ ሆሳዕና ያስፈረማቸውን ተጨዋቾች የማጣት ስጋት ውስጥ መግባቱ እየተነገረ ነው፡፡

የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጥቅማ ጥቅሞችና ቃል የገባውን ክፍያ በመፈፀም ለ1 አመት ማቆየቱን ያረጋገጠው ሀዲያ ሆሳዕና ለፋሲል ከነማ እንደፈረመው በረከት ደስታና ኢትዮጰያ ቡና እንዳቀናው አበበ ጥላሁን ቀሪ ተጨዋቾቹን የማጣት ስጋት ውስጥ መግባቱን የክለቡ ታማኝ ምንጮች በተለይ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚሉት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ተከትለው ወደ ሆሳዕና ባቀኑት ተጨዋቾች መሀል ዳዋ ሆቴሳና ምኞት ደበበ ቃል የተገባልንን ክፍያ አልተፈፀመልንም በሚል ክለቡን ለመልቀቅና ወደ ሌላ ክለብ ለመጓዝ ማቀዳቸው እየተነገረ ነው ሁለቱም ተጨዋቾች “ክለቡ ቃል የገባልንን ሊፈፅምልን ካልቻለ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሄደን አንፈርምም ወደ ሌላ ክለብ ለመሄድ እንገደዳለን” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ከአዳማ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ያቀኑት ተጨዋቾች ክፍያ ባለመፀሙና የተገባላቸው ቃል ባለመከበሩ ቅሬታ ውስጥም መግባታቸው ለሀትሪክ የደረሰው መረጃ ያስረዳል፡፡ በዚህ ቅሬታ ጉዳይ ምላሻቸውን የሰጡት የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ በበኩላቸው “ሀዲያ ሆሳዕና የተቻለውን እያደረገ ነው የትኛውም ክለብ ያላደረገውን ግማሽ ክፍያ በካሽ ሰጥተናቸዋል፤ ካሉን ተጨዋቾች ቅድሚያ ለነርሱ ሰጥተናል በቀጣይ ወር ሙሉውን እንጨርሳለን ይህንንም ነግረናቸዋል፤ ከዚህ በላይ ምን ይጠበቅብናል?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ መላኩ እንደሚሉት “የክለቦች ፋይናንስ የሚመጣው ከመንግሥት ነው ዞኑ ያቀረበው የክልል ጥያቄ ተመልሶለት ሙሉ ሃሣቡ በዚህ አደረጃጀት ላይ በመሆኑ ባለው ነገር እያመቻቸን እነሱን ለማስደሰት እየጣርን ነው ሙሉ በሙሉ የአመቱን ክፈሉ ሲሉን ግን ይከብዳል?” ጠብቁን ይስተካከላል እያልናቸው ነው፡፡የሌሎቹም ተጨዋቾች ተሰርቶላቸዋል ከሁሉም በላይ ግን እንደኛ በካሽ የሰጠ የለም በቼክ ብቻ ነው ይህን ማወቅ አለባቸው” በማለት የክለቡን አቋም ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport