ሀድያ ሆሳዕና እያስመዘገበ ካለው ደካማ ውጤት የተነሳ ከዋና አሰልጣኙ ካሊድ መሐመድ ጋር ሊለያይ የሚችልበትን ቅድመ ሁኔታ አውቀናል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ 2008 ላይ የመሳተፍ በለስ ቀንቶት በዛኑ አመት መጨረሻ ላይ በአሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ እየተመራ ከሊጉ መውረድ የቻለ ሲሆን አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሊጉ ከመለሱት በኋላ በፕሪምየር ሊጉ ያለፉትን አመታት እየተሳተፈ ይገኛል። በቀደሙት አመታት ከክፍያ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ከሚነሳባቸው እና በድግግሞሽ በሜዳና ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ሲታመስ እንመለከተው የነበረው ይህ ክለብ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ግን ከሚነሱበት ጉዳዮች መጠነኛ መሻሻሎችን አሳይቷል። በያዝነው የውድድር ዘመን ባለፈው አመት የአሰልጣኝ ግርማ ታደሠ ረዳት የነበሩትን ካሊድ መሐመድን በመንበሩ በመሾም አመቱን እያሳለፈ የሚገኙት ነብሮቹ በሊጉ ከተደረጉ 30 ጨዋታዎች 35 ነጥብን በመሰብሰብ 15ኛ ደረጃ ላይ በአሁኑ ሰዓት ለመቀመጥ ተገደዋል።
ለውጤት መጥፋቱ እንደ ካርድ እና የተጫዋቾች ጉዳት በምክንያትነት ተደጋግሞ ቢነሳም ክለቡ በተቃራኒው እያስመዘገበው ከሚገኘው ውጤት አንፃር አሰልጣኝ ካሊድ መሐመድ እና ሀድያ ሆሳዕና ሊለያዩ የሚችሉበትን መንገድ አውቀናል። አሰልጣኙ ትላንት ከወላይታ ድቻ ከገጠማቸው ሽንፈት ባሻገር በቀጣይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በ31ኛው ሳምንት የሚኖራቸውን ጨዋታ ማሸነፍ የማይችሉ ከሆነ ብቻ የአሰልጣኙ እና የክለቡ ስንብት የሚረጋገጥ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ