የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች በጋራ ያዘጋጁት ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በፕሪሚየር ሊጉ ለዘጠኝ እንዲሁም በከፍተኛ ሊጉ ደግሞ ለስምንት ክለቦች የስፖርት ትጥቅ አቅራቢ የሆነው ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች በመዲናዋ ለሚገኙ ክለቦች በትብብር ያዘጋጁት የስፖርት ማርኬቲንግ የግንዛቤና ልምድ ልውውጥ በዛሬው ዕለት በቤስት ዌስተርን ሆቴል ተጀምሯል ።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው ፕሮግራም ላይ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ክለቦች የተገኙ ተወካዮች የተሳተፉበት ሲሆን በጠዋቱ ፈረቃ ከስፖርት ማርኬቲንግ ከሰአት ደግሞ ከስፖርት ስፖንሰርሺፕ ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ገለፃ እና ውይይቶች ተካሂደዋል ።

በጠዋቱ ፈረቃ የድሬዳዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የማርኬቲንግ ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ፍፁም ክንደሼ ስለ ስፖርት ማርኬቲንግ ገለፃ ከተደረገ በኋላ ከተሰብሳቢዎች ጥያቄዎች ተነስተው በአቶ ፍፁም ክንደሼ ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ከክለቦች ተወክለው በመጡት ተወካዮች አማካኝነት ከዚህ ቀደም ከስፖርት ማርኬቲንግ ጋር በተያያዘ እንዴት እየሰሩበት እንዳለ እና ያላቸውን ልምድ ለመድረኩ አካፍለዋል ።

በከሰአቱ ፕሮግራም በአቶ ፍፁም ክንደሼ ስለ ስፖርት ስፖንሰርሺፕ ገለፃ ከተደረገ በኋላ በስብሰባው የተገኙትን ሰዎች በአምስት ምድብ በመከፋፈል በስፖርት ስፖንሰርሺፕ ዙሪያ አጠር ያለ ፕሮፖዛል ሰርተው እንዲያቀርቡ ተደርጓል ።

ከየምድቡ በተወከሉ አንድ አንድ ሰዎችም የሰሩትን ፕሮፖዛል በመድረኩ ካቀረቡ በኋላ አቶ ፍፁም ክንደሼ በቀረቡት ውይይቶች ላይ እና ከቀረቡት ፕሮፖዛሎች በመነሳት የተወሰኑ ሀሳቦችን አቅርበው የዛሬው ስልጠና ተጠናቋል ።

ከቀረቡት ፕሮፖዛሎች የተሻለ ተብሎ ለተመረጠው የጎፈሬ ትጥቅ አምራች በነገው ዕለት ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል ።

ስልጠናው በነገው ዕለት ከተካሄደ በኋላ ፍፃሜውን የሚያገኝ ይሆናል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport